የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አግተው ለኦነግ ሸኔ አመራሮች ሰጥተዋል በተባሉ ተከሳሾች ላይ ትዕዛዝ ተሰጠ

ዓቃቤ ሕግ ኦነግ ሸኔን ‹‹አሸባሪ›› በማለቱ መቃወሚያ ቀረበበት

በጥቅምትና በኅዳር ወራት 2012 ዓ.ም. በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተፈጥሮ የነበረውን ዘርን መሠረት ያደረገ ግጭት በመፍራት ከደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመሄድ ላይ የነበሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ተማሪዎችን አስገድዶ በመጥለፍ፣ ለኦነግ ሸኔ አመራሮች አስረክበዋል ተብለው ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ክስ የተመሠረተባቸው ዘጠኝ ተጠርጣሪ ተከሳሾች ላይ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡

ክስ ከተመሠረተባቸው 17 ተጠርጣሪዎች መካከል በእስር ላይ ሆነው ክሳቸውን እየተከታተሉ ያሉት ዘጠኝ ግለሰቦች ሲሆኑ፣ የተለያዩ ትዕዛዞችን የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሰው መግደልና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ሐምሌ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ባስቻለው ችሎት መዝገቡ ቀጥሮ የነበረው፣ ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. በችሎት ላልተገኙ ተከሳሾች ፖሊስ የክስ ቻርጅ እንዲያደርሳቸው ማድረጉን ለማረጋገጥና ክሱን በንባብ ለማሰማት ነበር፡፡ ፖሊስ ለተከሳሾቹ የክስ ቻርጁን እንዳላደረሰ በመግለጽ ለቀጣይ ቀጠሮ እንዲያደርስ በድጋሚ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ዓቃቤ ሕግ ካመለከተ በኋላ፣ ፍርድ ቤቱ ክሱን በችሎት ለተገኙት ዘጠኝ ተከሳሾች በንባብ አሰምቷል፡፡ ክሱ ግልጽ ስለመሆኑ ለተከሳሾቹ በአስተርጓሚ አስጠይቆ ‹‹ግልጽ ነው›› ብለዋል፡፡

በክሱ ላይ ሰባት ተከሳሾች በግል ባቆሙት ጠበቃቸው አቶ ሊበን አብዲ አማካይነት የመጀመርያ ደረጃ መቃወሚያ ሲያቀርቡ፣ ሁለት ተከሳሾች ደግሞ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

የተከሳሾቹ ጠበቃ ባቀረቡት የመጀመርያ ደረጃ መቃወሚያ እንዳብራሩት በደንበኞቻቸው ላይ የተመሠረተው የሽብርተኝነት ድርጊት ወንጀል ክስ፣ ‹‹የሽብርተኝነት ወንጀልን አያቋቁም›› ብለዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ ተማሪዎችን በማገት ለኦነግ ሸኔ ማስረከባቸውን አረጋግጫለሁ ቢልም፣ ያቀረበው ፍሬ ነገር ከፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3(3) ድንጋጌ ጋር እንደማይጣጣም ጠቁመዋል፡፡ የአዋጁ ድንጋጌ እንደሚያስረዳው የሽብር ድርጊት ተፈጽሟል የሚባለው የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም የ‹አይዶሎጂ› ዓላማን ለማራመድና በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ዕገታ ወይም ጠለፋ ከተፈጸመ የሚል መሆኑን ጠበቃው ጠቁመዋል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 2(5) ድንጋጌ መሠረት ‹‹ዕገታ ወይም ጠለፋ›› ተፈጽሟል የሚባለው ሰውን በመያዝ ለመልቀቅ ቅድመ ሁኔታን በማስቀመጥ መንግሥት አንድ ነገር ካላደረገ በተያዘው ሰው ላይ ከባድ ጉዳት እንደሚደርስ ዛቻ ከተፈጸመ ብቻ መሆኑ የተደነገገ ቢሆንም፣ ተከሳሾቹ ግን ያንን ስለማድረጋቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ አለመግለጹንና ይህም ተከሳሾች ፈጽመውታል ተብለው የተከሰሱበትን የሽብር ድርጊት ወንጀል ማቋቋሚያ ፍሬ እንደማያሟላ በመቃወሚያው አስረድተዋል፡፡

ጠበቃው ሌላው ያቀረቡት መቃወሚያ ደንበኞቻቸው የተከሰሱበት በተሻረ አዋጅ መሆኑን ነው፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 የሽብር ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 መተካቱንና ሙሉ በሙሉ መሻሩን ጠቁመው፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2) ድንጋጌ መሠረት ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ የወጣ ሕግ ለተከሳሹ ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ አዲሱ ሕግ ተፈጻሚ እንደሚሆን ስለተደነገገ፣ ዓቃቤ ሕግ በአዲሱ አዋጅ መሠረት ክሱን አሻሽሎ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ ተከሳሾቹን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(4) ሥር የተሰጣቸውን መብት የሚጋፋ መሆኑንም ጠበቃው አስረድተዋል፡፡ ተከሳሾች የምስክሮችን ስም ዝርዝር የማወቅ መብት ቢኖራቸውም፣ የምስክሮችን ደኅንነት ለመጠበቅ የወጣውን አዋጅ 699/2003 አንቀጽ (4)ን በመጥቀስ እንዳይሰጣቸው ማድረጉን ተቃውመዋል፡፡ አዋጁ የሚያገለግለው ክሱ ያለ ምስክሩ ቃል ውጤት አያመጣም ሲባልና አደጋው ከባድ መሆኑ ሲረጋገጥ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ ይህንን ሳያረጋግጥና መንግሥትም ምስክሮችን የመጠበቅ አቅሙ እያለው መከልከሉን ተቃውመዋል፡፡ በተከሳሾቹ ላይ የተሰበሰበው የሰነድ ማስረጃ በኦሮሚኛ 40 ገጽ ሆኖ ሳለ፣ ለተከሳሾቹ ተተርጉሞ የተሰጣቸው ግን ሁለት ገጽ ብቻ በመሆኑ ተስተካክሎ እንዲደርሳቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

በመጨረሻም ተከሳሾቹ ተማሪዎቹን ለኦነግ ሸኔ አሸባሪ ቡድን አሳልፈው እንደሰጡ ዓቃቤ ሕግ ቢገልጽም፣ ‹‹አሸባሪ›› የሚለውን ስያሜ መስጠት የሚችለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሆኖ ሳለ ዓቃቤ ሕግ ግን ቃላሉን በመጠቀም ክስ በመመሥረቱ፣ ስያሜውን አስተካክሎና ክሱን አሻሽሎ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ ሁለት ተከሳሾች ደግሞ የተጠቀሰባቸው የወንጀል ሕግ ዋስትና እንደማይከለክል አስረድተው የዋስ መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤት የተከሳሾቹ የመጀመርያ የክስ መቃወሚያ ለዓቃቤ ሕግ እንዲደርሰው ካደረገ በኋላ የመቃወሚያ መልሱን እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት፣ በመዝገቡ ላይ ብይን ለመስጠት ለነሐሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.