ኦነግ ፡ “ስለመግለጫው አላውቅም፤ አላማውም ምን እንደሆነ አይገባኝም” አቶ ዳውድ ኢብሳ

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ትናንት ሰኞ በድርጅታቸው አመራሮች አዲስ አበባ ውስጥ ስለተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ለቢቢሲ ተናገሩ።

አቶ ዳውድ፤ “ስለ መግለጫው አላውቅም። አጀንዳውም፣ አላማውም ምን እንደሆነ አይገባኝም” ሲሉ እንደግንባሩ ሊቀመንበርነታቸው ምንም እንደማያውቁ ገልጸዋል።

በግንባሩ ስም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት ከፍተኛ አመራሮች አቶ አራርሶ ቢቂላ ምክትል ሊቀመንበር፣ አቶ ቶሌራ አደባ ቃል አቀባይ እና አቶ ቀጀላ መርዳሳ በጋራ ሆነው ሲሆን ኦነግን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አመራሮቹ እንዳሉት ግንባሩ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ቢወስንም አመራሮቹና አባላትን በማሰር እንዲሁም ስሙን የማጠልሸት ዘመቻ እየተካሄደበት መሆኑን ጠቅሰው በተጨማሪም በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላቱ እንደታሰሩበትም አመልክተዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ለደኅንነታቸው ሲባል በጸጥታ ኃይሎች ከቤታቸው እንዳይወጡ በተደረገበት ጊዜ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በጽህፈት ቤቱ ስብሰባ ማካሄዳቸውን በተመለከተ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።

ይህንንም በተመለከተ የኦነግ የሕግና የቁጥጥር ኮሚቴ የማጣራት ሥራ እንዲያከናውን እንደሚደረግ አቶ ዳውድ ኢብሳ ተናግረው ቀደም ያለው ስብሰባ ጉዳይ እስኪጣራ ድረስ መግለጫ መስጠት መከልከሉንና የአሁኑም ጋዜጣዊ ጉባኤ ከዚህ ጋር የተቃረነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አቶ ዳውድ ኢብሳ ስለቆዩበት ሁኔታና ስለድርጅታቸው ይናገራሉ
በአቶ ዳውድ ኢብሳ ቤት አካባቢ እየተከናወነ ያለው ነገር ምንድን ነው?
የእሁዱ ስብሰባና በኦነግ አመራር አባላት መካከል የተፈጠረው ተቃርኖ
“የተደረገው ስብሰባ በጣም የተምታታ ስለሆነ የሕግና የቁጥጥር ኮሚቴው እስከሚያጣራ ምንም አይነት መግለጫ እንዳይሰጥ ተብሎ አቁሟል። እነሱም ምን መግለጫ እንደሚሰጥ አናውቅም ብለው መልሰውልኛል። የማምታታት ሥራ እየተሠራ ነው” ሲሉ አቶ ዳውድ ሁኔታውን ገልጸዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ለሁለት ተከፍሏል በሚል በስፋት እተነገረ ስላለው ጉዳይ በተመለከተም ሊቀ መንበሩ ግንባሩን ለማዳከም “አሁን ባለው የፖለቲካ ሁኔታ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ኢላማ ውስጥ ነው” ብለዋል።

“መንግሥት በራሱ የዴሞክራሲ ሂደት፣ በሰላም መንቀሳቀስ ሲያቅተውና ተፎካካሪ ፓርቲ ሲበረታበት በገንዘብም ይሁን በማስፈራራትም በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ጣልቃ ይገባል” ሲሉ ሊቀ መንበሩ አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደምም መሰል ጣልቃ ገብነት በግንባራቸው ላይ ሲሞከር እንደነበረ የተናገሩት አቶ ዳውድ፤ “ይሄ አሁንም የማይደረግበት ምክንያት የለም። ብዙ ገንዘብ ነው የሚረጨው” ሲሉ ጥረቱ በገንዘብ ችምር የሚደገፍ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሳምንታት በፊት ከቤታቸው እንዳይወጡ የተደረጉትም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ገልጸው ”ስልኬን ያፈኑበትም የዚህ ኦፕሬሽን (ተልዕኮ) አካል ነው” ሲሉ እየደረሰብን ነው ያሉትን ጫና ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በግንባሩ ጽህፈት ቤት ያለ ሊቀመንበሩ የተካሄደውን ስብሰባ ተከትሎ የሚቃረኑ አስተያየቶች የተሰነዘሩ ሲሆን የስብሰባው ተሳታፊዎች ጉዳዩን አቶ ዳውድ እንደሚያውቁት ቢናገሩም እሳቸው ግን የሚያውቁት ነገር እንዳልነበረ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሰኞ ዕለት በአዲስ አበባው ሒልተን ሆቴል ውስጥ የተሰጠውን መግለጫ በሚመለከተም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር የሚያውቁት ነገር እንደሌለና በተለያዩ መንገዶች ጫና እየገጠማቸው መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አቶ ዳውድ ኢብሳ ከቤታቸው መውጣት ባልቻሉባቸው ጊዜያት የተካሄደውን የግንባሩን አመራሮች ስብሰባ ተከትሎ አዲስ ሊቀመንበር ስለመመረጡ እና ድርጅቱ ለሁለት ስለመከፈሉ ወሬዎች ሲናፈሱ ቢቆዩም ሁሉም አመራሮች እነዚህ ወሬዎች ሲያስተባብሉ ቆይተዋል።

ኦነግ ለኦሮሞ ሕዝብ መብት ከሚታገሉ ድርጅቶች ቀዳሚው ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት ከግንባሩ እራሳቸውን የለዩ አባላቱ በኦሮሞ ስም የተለያዩ ድርጅቶችን በማቋቋም ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።

አሁን በአቶ ዳውድ ኢብሳ ሊቀመንበርነት የሚመራው ግንባር ከሌሎች የኢትዮጵያ የፖለቲካ ቡድኖች ጋር በሕገ ወጥነት ተፈርጆ ለበርካታ ዓመታት መቀመጫውን አሥመራ ውስጥ አድርጎ የትጥቅ ትግል ስልትን ሲያራምድ ቆይቷል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለውጥ ከተካሄደ በኋላ ኦነግና ሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች ከአገሪቱ የሽብር ዝርዝር ውስጥ እንዲወጡ ተደርጎ ወደ አገር ቤት ተመልሶ በሰላማዊ የፖለቲካ መድረክ በመሳተፍ ላይ ይገኛል።

BBC

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.