ኢትዮጵያ ፡ መንግሥትንና ህወሓትን የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት እንዲያሸማግሉ ክራይስስ ግሩፕ ሐሳብ አቀረበ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የሠላም ኖቤል ተሸላሚው ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታራቂና የሚያቀራርቡ ንግግሮቻቸውን ወደ ተግባር እንዲለውጧቸው ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ጠየቀ።

ቡድኑ በተጨማሪም ያለውን ውጥረት ለማርገብ አስፈላጊ ከሆነም የአፍሪካ ሕብረት ወይም የአፍሪካ መሪዎች በማሸማገሉ በኩል ተሳትፎ ሊያደርጉ ይችላሉ ከማለት በተጨማሪ በተለይ የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር የሆኑት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ ብሏል።

ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ፣ በተለይም የትግራይንና የማዕከላዊውን መንግሥት ፍጥጫ ትኩረት ሰጥቶ በገመገመበት ባለ 14 ገጽ ሰነድ እንደጠቀሰው በኦሮሚያ ክልል የሰላም መደፍረስና የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳደር ጋር የገባበት ፍጥጫ በንግግር ሊፈታ ይገባል ሲል መክሯል።

አለበለዚያ ግን ተስፋ የተጣለበት ፖለቲካዊ ሽግግሩ እንቅፋት ሊገጥመው ይችላል ሲል ስጋቱን አንጸባርቋል።

በኦሮሚያ ከተሞች በቅርቡ የታዩት ሠላም መደፍረሶች ኢትዮጵያ የጀመረችውን ፖለቲካዊ ሽግግር አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችል አሳሳቢ ቀይ መብራቶች ናቸው ብሏል ድርጅቱ።

የትግራይ ክልል ልሂቃን ክልላዊ ራስን የማስተዳደር መብት በክልልላችን ምርጫ ማካሄድ ሙሉ መብት ያጎናጽፈናል የሚል አቋም እንደያዙና የፌዴራል መንግሥት በበኩሉ ሕገ መንግሥቱ ይህን እንደማይፈቅድ በመግለጹ ፍጥጫው መከሰቱን ካብራራ በኋላ ሁለቱም ወገኖች ፖለቲካዊ ጡዘቶችን እንዲያረግቡ ተማጽኗል።

ሁለቱም ወገኖች የያዙትን አቋም ያስቀመጠው ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ማዕከላዊ መንግሥት በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ላይ ለማሳደር እየሞከረ እንደሆነ የጠቀሰ ሲሆን ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ በበኩሉ ምርጫ አካሄዳለው ብሎ ዝቷል።

ሆኖም እንደ ክራይስስ ግሩፕ ከሆነ ሁለቱም የያዙት አቋም አያዋጣም። የሁለትዮሽ ንግግርንም አያበረታታም።

ሁለቱም “የገደል ጫፍ ላይ ናቸው” ያለው ድርጅቱ በብልጽግናና በህወሓት መካከል ያለው መጠላላትና ሽኩቻ በመጨረሻ የአገር ተስፋን የሚያጨልም ነው ብሎታል።

ሰነዱ የትግራይ ልሂቃን ከምርጫ ጋር በተያያዘ ካሉ ሁኔታዎች ለማትረፍ የሚያደርጉት ሙከራ አደገኛ ነው ካለ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም የአገር መሪና የሠላም ኖቤል ተሸላሚ እንደመሆናቸው ይበልጥ እርሳቸው የሞራል ልዕልናው ኖሯቸው አስታራቂ መንፈስ ያለው አንደበታቸውን (ንግግሮቻቸውን) ወደ ተግባር እንዲመነዝሩ ጠይቋል።

አርማ

ለተቃዋሚዎችም ሆነ አሁን ከእርሳቸው በተቃራኒ ለቆመው የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ፓርቲ የእርቅ ዕድሎችን እንዲያመቻቹም አሳስቧል።

በማዕከላዊው መንግሥትና በህወሓት መካከል ያለውን ፍጥጫና መከራር ለማለዘብ በሰኔ ወር የሽማግሌዎች ቡድን ሙከራ ጀምሮ እንደነበር ያስታወሰው ሰነዱ፤ ሆኖም ሁለቱም ባላቸው ግትር አቋም የተነሳ ሽምግልናውን ከበድ ላለ አካል ማስተላለፍ ሳያስፈልግ አይቅርም ብሏል።

ምናልባት ለህወሓትና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅርብ የሆኑ ስመጥር የአፍሪካ መሪዎች በሽምግልናው ላይ ቢገቡ መልካም ይመስላል ሲል ሃሳብ አቅርቧል።

ሆኖም ግን የሚመጡት ሸምጋዮች የኢትዮጵያ መንግሥታት ለውጭ ጣልቃ ገብነት ያላትን አሉታዊ አመለካት ከግምት በማስገባት ከአፍሪካ መሪዎች ሸምጋይ የሚሆኑት ርዕሳነ ብሔራት ብልህና ስልተኛ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ከወዲሁ አሳስቧል።

በዚህ ረገድ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበርና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ አዎንታዊ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ተስፋ አድርጓል፤ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ።

በሽምግልና የሚሳተፉ ተሰሚነት ያላቸው የአገር መሪዎች መጀመርያ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ወታደራዊ እርምጃ ቀርቶ ምንም አይነት የፋይናንስ ጫና በህወሓት ላይ እንዳያሳድር መምከር ይኖርባቸዋል ብሏል ድርጅቱ።

በተመሳሳይ መቀለ ያለውን አመራር ምርጫ የማካሄዱን ሐሳብ እንዲተው ማግባባት ይጠበቅበታል።

ሆኖም ድርጅቱ ሁለቱ ወገኖች ጽንፍ በመያዛቸው አስታራቂና አማካይ መንገድ ማግኘት ቀላይ እንደማይሆን ይጠበቃል ብሏል።

የትግራይ ክልል ምርጫ የማካሄድ ሙሉ ሥልጣን አለኝ ካለ ሁሉንም የሕግ ሂደቶች አሟጦ መጠቀም ይኖርበታል ይላል።

ለምሳሌ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉም የመስጠት ስልጣን ስላለው ክልሎች በራሳቸው ምርጫ ማካሄድ አለባቸው ወይስ የለባቸውም በሚለው ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥ ክልሉ ይግባኝ እንዲልና የሕግ መስመርን ብቻ እንዲከተል መክሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የአራት ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት የሆነውና ለሦስት አስርት ዓመታት ያህል አገሪቱን ያስተዳደረው ገዢ ፓርቲ ኢህአዴግ ከስሞ አንድ ወጥ አገራዊ ፓርቲ እንዲመሰረት አድርገዋል።

ከኢህአዴግ መክሰም በኋላ አዲስ ወደ ተመሰረትው የብልጽግና ፓርቲ መግባት ያልፈለገው በአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የነበረው ህወሓት ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር አለመግባባት ውስጥ ቆይቷል።

በተለይም በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው አገራዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለሌላ ጊዜ መተላለፉን ህወሓት አምርሮ የተቃወመው ሲሆን በሚያስተዳድረው ክልል ውስጥ የተናጠል ምርጫ አካሂዳለሁ በማለቱ አለመግባባቱ እየተባባሰ ሄዷል።

5 COMMENTS

  1. የእብድ ገላጋይ ድንጋይ ያቀብላል ይላሉ አበው፡፡ በምን ሂሳብ ነው የሚታረቁት? ጭራሽ የሚያገናኛቸው ነገር የለላቸውን ባላንጣዎች ኑና ታረቁ ማለት በጊዜና በሃብት ላይ መቀለድ ነው፡፡ ወያኔ እርቅ ሳይሆን ተለቅሞ እስር መውረድ ያለበት ቡድን ነው፡፡ ከጅምሩ የማፊያ ቡድን የሆነው ወያኔ እልፍ የትግራይ ልጆችን በበረሃ አፈር የመለሰባቸው ለእውነት ስለቆሙ ነበር፡፡ በትግራይ ህዝብ ስም ዘንተ አለም የሚነግደው ይህ ቡድን ለትግራይ ህዝብ ገዶት አያውቅም፡፡ አሁን ሳያስበው ከስልጣን ተሽቀንጥሮ መቀሌ ላይ የመሸገው ይህ ዘራፊ ቡድን የሚያደርገው ቢያጣ ሻቢያ መጣብህ፤ አማራ ከበበህ፤ የዶ/ር አብይ መንግስት ሊወርህ ነው እያለ የጦር ነጋሪት እየመታ ለመሆኑ ወታደራዊ ሰልፉና የፈጠራና በሃገሪቱ ላይ የሚያደርሰው ሰውር ሴራ አስረግጦ ያስረዳል፡፡
    ታዲያ እንዲህ ያለ ሃይልን እንዴት አድርጎ ነው ለድርድር የሚቀርቡት? በስብሰባ መካከል አሜን ብለው አይደል እንዴ መቀሌ ሲገቡ ሌላ ሃሳብ የሚያመነጩት? ወያኔ በዘሩ የሰከረ ሌሎችን ብሄር ብሄሮች ያሳከረ ሃገር ያፈረሰ የክልል ፓለቲካ አራማጅ ጭፍን ድርጅት ነው፡፡ ግን እኮ ፓለቲካ ወሽካቶችን ይወዳል፡፡ ለእውነት የቆሙትና ጥያቄ ያነሱት ዛሬ የት አሉ? ሌባውና ዘራፊው፤ ዘረኛውና በቋንጨራ የሰው አንገት የሚቀላው፤ ጀርመን ላይ ተቀምጦ ኢትዮጵያ ትውደም የሚል የኦሮሞ መንጋ ያፈራች ሃገር ናት፡፡ የአብሮ መኖር ስሌት ከፈረሰ ቆይቷል፡፡ ራሳችን ባናታልል መልካም ይመስለኛል፡፡ ሰው እንደ እንስሳት እየታደነ በእሳት በሚቃጠልባት መሬት ፍትህ ይኖራል ብሎ መገመት ፌዝ ነው፡፡ የኦሮሞ የፓለቲካ ወሽካቶች ከውጭ እስከ ሃገር ቤት አብደዋል፡፡ በሃሳብ ልዪነት በአሜሪካ ምድር ሴት ልጅን የሚደባደቡ የእነርሱ ሃሳብ ካልሆነ በስተቀር የሌላው እንዳይደመጥ የማይሹ ሾተላዪች ለሃገርም ለራስም አይጠቅሙም፡፡ ጥምር ህዝብ በሚኖሩባቸው ሃገሮች ተጠልለውና ተወልደው እየኖሩ ዛሬም ዘሩን እንደ ባቄላ የሚቆጥር ሽታ ቢስ ፓለቲካ ለሃገርም ለአለም አቀፋዊ እይታም ጭራሽ አይበጅም፡፡ የደቡብ አፍሪቃው መሪ ወያኔና የጠ/ሚ መንግስት እንዲያስታርቁ የሚባለውም ተንጋሎ መትፋት ነው፡፡ ደቡብ አፍርቃ ውስጥ አይደል እንዴ ሰው አንገቱ እየተቀላ የሚሞተው? ልክ እንደ ኦሮሞዎቹ መጤ ናቸው እየተባሉ ሞት የተፈረደባቸውን፤ የተዘረፉትን፤ እስር ቤት የተጋዙትን፤ የሞዛምቢክ፤ የዝምባብዌ፤ የኢትዮጵያ ዜጎችን እንደምሳሌ ማውሳት ይቻላል፡፡ የጥቁር ህዝብ ጠላቱ ራሱ ነው፡፡ ሌላው ሁሉ አሽንክታብ ማብዛት ነው፡፡ አስታራቂዎች ነን የሚሉም የራሳቸው የሆነ አጀንዳ አላቸው፡፡ ዛሬ በአረብ ሃይሎች የተከበበቸው ሃገራችን ኢትዮጵያ ገና አያሌ ፈተና ከውጭና ከውስጥ ይጠብቋታል፡፡ እንደ ተልባ ነዶ አንድ ጋ ሲጠብቅ ሌላ ጋ እያፈተለከ ያለው የጠ/ሚሩ የመደመር ሂሳብም በኦሮሞ ጭፍን ፓለቲከኞችና በወያኔ ሴራ ህዝባችን በየቀኑ እየገደለው ነው፡፡ ድረሱልን ሲባሉ ቆመው ያስገደሉት የኦሮሞ ፓሊሶች አሁን ቀዳሚ ሃዘን ደራሾችና ሲልላቸውም ከሞት ተራፊዎችን እያስፈራሩ እንደሚገኙ ከሚበተኑ ወረቀቶችና የስልክ እንዲሁም የቃል ማስፈራሪዎች መረዳት ይቻላል፡፡ ስለሆነም እብደቱ ቀጥሏል፡፡ ወደፊትም የሚያቆመው የለም፡፡ ጅልነት ነው የኦሮሞ ፓለቲከኞች ልባቸው ተቀይሮ ከሌላው ወገናችን ጋር አብሮ መኖርን ይሻሉ ብሎ ማመን፡፡ ስለዚህ ችግሩ መልክና ይዘቱን ቀይሮ እንደገና ብቅ ይላል፡፡ የገደለ በማይገደልባት ሃገር ማን ምንን ይፈራል፡፡ ወያኔ የትግራይን ህዝብ ለጦርነት ማነሳሳቱ ሂትለራዊ ወንጀል ነው፡፡ የትግራይ እናቶች ባለፈው በደል እንባቸው ሳይደርቅ እንደገና ልጆቻቸውን ለወያኔ ስልጣን እንዲገብሩ መገፋፋት ዋ ሰላም በስምሽ ስንት ግፍ ተሰራ የሚለውን የሃይለስላሴ ደስታን መጽሃፍ ያስታውሰኛል። በመጨረሻም እውቁ ኤርትራዊ ከያኔ የማነ ባሪያ የዘፈነውን አንድ ዘፈንም አስታወሰኝ። “ሃዘን ዋጋ ይብሉን” ፈልጉና ስሙት። ትልቅ ትምህርት አለው። ኢትዮጵያዊያን ከራሳቸው ጋር ነው መታረቅ ያለባቸው። ችግሩ እኛው ነን። ሌላ የውጭም ሆነ ሃገር በቀል ሽምግልና ጭራሽ አያስፈልግም። በቃኝ!

  2. በአንድ ሉአላዊ ግዛት ያለውን ሀገር በምን ሂሳብ ነው ሌላ ሀገር ያስማችሁ ብሎ ሀሳብ መስጠት? ከሀሳቡ ይልቅ ያለመውን ነገር መመርመር ያስፈልጋል። ስፔንና እንግሊዝ ባሸባሪዎች ሲናጡ ማን ወንድ ነው ላስማማችሁ ብሎ የሞከረው? አረ ተው ፈረንጆች ቀን ቢጥለንም ይህን ያህል አትናቁን አዱኛ ወርቁ እንዳለው መነሳታችን አይቀርም።

  3. ወይ እናንተ ፈረንጆች ህወአት ግራ ሲገባዉ እንዳይሞት አየር መስጠታችሁ ነዉ? እኛ ለእንግሊዝ/ለአሜሪካ/ለፈረንሳይ/ለጀርመን ሀሳባ ሰጥተናል እንዲህ ብታደርጉ ብለን? ምናለ ብትተዉን ቀጥሎ ደግሞ የግብረ ሰዶም ቤተ እምነት ይቋቋም ብላችሁ መጠየቃችሁ አይቀርም አረ ተዉን። እንዲህ አይነቱን ትያትር ትታችሁ ግብጽን አስታግሱልን እኛ ችግራችንን እንወጣዋለን እናንተ ካልገባችሁብን።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.