ለቸኮለ! የዛሬ ማክሰኞ መስከረም 12/2013 የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ላልተወሰነ ጊዜ የተራዘመው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ፣ ዘንድሮ እንዲደረግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ስብሰባው እንደወሰነ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡ ምክር ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው፣ ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ወረርሽኙን መከላከል ከሚያስችሉ ጥንቃቄዎች ጋር ምርጫውን ማድረግ ይቻላል በማለት ባቀረበለት የውሳኔ ሃሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ ነው፡፡ የውሳኔ ሃሳቡ ባንድ ተቃውሞ እና በ6 ድምጸ ተዓቅቦ ነው የጸደቀው፡፡
2. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ የአዳዲስ ሚንስትሮችን ሹመት በ5 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ እንዳጸደቀ ከምክር ቤቱ ፌስቡክ ገጽ ተመልክተናል፡፡ ካንድ ወር በፊት ተሹመው ዛሬ ሹመታቸው የጸደቀላቸው፣ መከላከያ ሚንስትር ቀንዓ ያዴታ፣ የማዕድን እና ኢነርጅ ሚንስትር ታከለ ኡማ፣ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ሳሙዔል ሁርካቶ እና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ናቸው፡፡ ምክር ቤቱ 50 የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እና 40 የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞችን ሹመትም በአብላጫ ድምጽ ያጸደቀ ሲሆን፣ ዳኞቹም ምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡
3. ተቃዋሚ ፖለቲከኛው ልደቱ አያሌው በ100 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ የምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደወሰነ ኢትዮ ኤፍኤም የፓርቲያቸውን የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሃላፊዎችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ተከሳሹ የጦር መሳሪያ አስተዳደር አዋጅን በመተላለፍ የተመሠረተባቸውን ክስ በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ወስኛለሁ- ብሏል ፍርድ ቤቱ፡፡ ችሎቱ ክሱን ለማየት ለመስከረም 20 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
4. ዐቃቤ ሕግ በባልደራስ ፓርቲ ሊቀመንበር እስክንድር ነጋ እና ሌሎች 7 ተከሳሾች ላይ የከፈተውን ክስ እንደገና አብራርቶ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት ያንድ ሳምንት ጊዜ እንደሰጠው አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል፡፡ ተከሳሾቹ ቀስቅሰውታል በተባለው ሁከት፣ የት ቦታ፣ መቼ እና ምን ዐይነት ጉዳት እንደደረሰ እና ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በወንጀል ድርጊቱ ምን ሚና እንደነበራቸው ተለይቶ እና ተብራርቶ እንዲቀርብለት ነው ችሎቱ ትዕዛዙን የሰጠው፡፡
5. በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የተዘጉ ትምህርት ቤቶች በሚከፈቱበት ቀን እና አከፋፈታቸው ላይ ትምህርት ሚንስቴር ከክልል ትምህርት ቢሮዎች ጋር ሲመክር እንደዋለ ፋና ብሮድካስት ዘግቧል፡፡ የምክክር መድረኩ ለ8ኛ እና 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናዎች የሚሰጡበትን የጊዜ መርሃ ግብርንም ይወስናል፡፡ ከምክክሩ በኋላ፣ የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱበትን ቀን እና አከፋፈታቸውን ነገ ይፋ እንደሚያደርግ ትምህርት ቤት አስታውቋል፡፡
6. የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለወላይታ ዞን የቀድሞ አመራሮች የፈቀደውን ዋስትና ሽሮ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጥ ከፖሊስ የቀረበለትን ይግባኝ ዛሬ ሲያዳምጥ እንደዋለ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል፡፡ የተጠርጣሪ ጠበቆች እና ዐቃቤ ሕግ መከራከሪያቸውን ለችሎቱ አሰምተዋል፡፡ ከ20ዎቹ ተጠርጣሪዎች 9ኙ ችሎት የቀረቡ ሲሆን፣ የዞኑ የቀድሞ ዋና አስተዳዳሪ ዲጋቶ ኩምቤ ግን አልተገኙም፡፡ የወላይታ ሀገር ሽማግሌዎች ጉዳዩን በሽምግልና ለመጨረስ እንደጠየቁ ዘገባው አክሎ ጠቅሷል፡፡
7. 251 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ዛሬ ከሳዑዲ ዐረቢያ ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡ ስደተኞቹ በሳዑዲ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የቆዩ ናቸው፡፡
8. ኬንያ ሕገወጥ ንግድን ለመቆጣጠር በሞያሌ እና ኬንያዋ መርሳቢት ክፍለ ሃገር አዋሳኝ ላይ ያለ ሕገወጥ መተላለፊያን እንዳጠረች ስታንዳርድ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ አጥሩ 10 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ሲሆን፣ ወደ 56 ኪሎ ሜትር ለማሳደግ ዕቅድ አለ፡፡ መተላለፊያው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ አደንዛዥ ዕጥ፣ ጦር መሳሪያ እና ኮንትሮባንድ ሸቀጦች የሚገቡ የሚወጡበት ነው፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.