የዶክተር አብይ INSA … ሰብዓዊ መብት ጥሰት – ሳሙኤል ሃ

የዶክተር አብይ INSA … ሰብዓዊ መብት ጥሰት
Samuel Ha
ከሰሞኑ “አፈትልኮ ወጣ” በሚል የተሰራጨው አንድ የINSA የቀድሞ ባለሙያ የነበረ ግለሰብ ከኢሳት ጋዜጠኛ ከነበረው አበበ ገላው ጋር ከበርካታ ዓመታት በፊት ያደረገው እና በየኔታ በሚባል ዩ ትዩብ የተለቀቀው 55 ደቂቃዎች የወሰደ ቃለምልልስ ውስጥ የተረዳሁት ሁለት አበይት ነገሮች የሚከተሉት ናቸው።
የመጀመሪያው እና ዋናው አቶ #አብይ_አህመድ (የዛሬው ጠቅላይ ሚኒስትር) በዋነኛነት እና አቶ #ሲሳይ_ቶላ (ምናልባት የዛሬው የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ መሆን አለባቸው ) የተባሉ ሁለት ሃላፊዎች በዳይሬክተርነት ይመሩት የነበረው የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የተባለ መስሪያ ቤት ኢትዮጵያውያን መረጃ የማግኘት መብታቸውን በማፈን ፣ ሃሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን በማገድ ፣ ይህንንም በማድረግ ለብዙዎች ከሥራ መባረር ፣ ከሃገር መሰደድ ፣ በእስር መንገላታት እና ሞት ምክንያት በመሆን ለአፋኝ ሥርዓት በመሣሪያነት በማገልገል በሕዝብ ላይ የፈፀመውን ከባድ ወንጀል ነው።
የኢትዮጵያውያን ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ እና መረጃ የማግኘት መብት ማፈን አይገባንም በማለት ሃሳብ የሚያቀርቡ የድርጅቱ ከፍተኛ ባለሙያዎችን ከሥራ ማባረር ማሰር እና ማንገላታት ይፈፀም የነበረው በተለይ በአቶ አብይ አህመድ አማካይነት መሆኑን ቃለምልልሱን የሰጡት ግለሰብ ተናግረዋል ። ቃለምልልስ የሰጠው የቀድሞው INSA ባለሙያ አቶ አብይ የነበራቸውን የማኔጅመንት ችሎታ ፣ አሰራሮችን ፈጥነው የመረዳት ችሎታ ማድነቃቸውን የገለፁ ሲሆን ለተለየ ብሔር የማድላት አካሄድ አስተውለውባቸው እንደማያውቅ ምስክርነቱን የሰጠ ቢሆንም ከ 46:20 እስከ 47:50 ደቂቃዎች እንደሚሰማው “ምሁራኑን አንዲሸሹ የሚያደርገው … እሱ (ዶክተር አብይ) ነው ችግር የሆነብን” በማለት ገልፀዋል።
ሁለተኛው እና በቃለምልልሱ ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው ነገር ግን እኔ መታዘብ የቻልኩት ጉዳይ የኢትዮጵያን የውጭ ጠላቶች በመሰለል እና ሊያደርሱ ይችሉ የነበረውን ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል መረጃ በረቀቀ የደህንነት ቴክኖሎጂ በመታገዝ ለሃገሪቱ የደህንነት ምክር ቤት በማቅረብ ሀገርን ከጥፋት መታደግ የሚያስችል ብቃት መገንባቱን ነው። የሚያስመሰግን ተግባር ነው።
ለማጠቃለል…..
የዛሬው ዶክተር አብይ ትላንት ኢትዮጵያውያን መረጃ የማግኘት መብታቸውን ማፈኑ እና ሃሳባቸውን በነፃነት እንዳይገልፁ ማድረጉ በየትኛውም መመዘኛ ትክክል አይደለም። ብዙዎች የህይወት ዋጋ የከፈሉት ያን በጊዜው በዶክተር አብይ መሪነት ሲካሄድ የነበረውን ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመቃወም ነበር። ዛሬ ለሳቸው ያለን ጭፍን ፍቅር የቀድሞውን ስህተት ምናልባትም ወንጀል ሊያፀዳ አይችልም። “INSA በነበርኩኝ ጊዜ አውቄው የፈፀምኩት ስህተት የለም” በሚል ዶክተር አብይ ሲናገሩ ሰምቻለሁ። የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስህተት ብቻ ሳይሆን ወንጀልም መሆኑን ለርሶ መንገር አይገባኝም። በጊዜው ያምኑበት ለነበረው ዓላም ሲሉ የተለየ አመለካከት የነበራቸውን ኢትዮጵያውን ዜጎች ሰብዓዊ መብት መዳፈርዎ ትክክል የሚሆነው በአፋኝ መንግሥት እይታ ብቻ ነው።
እኔን ጨምሮ ብዙዎች ዶክተር አብይ ኢትዮጵያ ከገባችበት ቅርቃር አንፃር እየሄዱቡት ያለው መንገድ በአንጻራዊነት ለጊዜው የተሻለ ነው ብለን እናምናለን። ይበልጥ ጠንክረው የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን በመገንባቱ ሂደት ታሪክ የማይረሳው አሻራ ጥለው እንዲያልፉ እንፈልጋለን። በጭፍን ፍቅር ታውረን ቀድሞ የINSA ሃላፊ በነበሩ ጊዜ እንዳደረጉት የኢትዮጵያውያንን ድምፅ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ እንዲያፍኑ ግን ልናበረታታቸው አይገባም። በዚህ ረገድ ቀይ መስመር ማለፍ መሆኑን ልናሳውቃቸው ይገባል።

1 COMMENT

  1. INSA did not harm a single Ethiopian person while it was under Dr. Abiy Ahmed. Not one person came forward in social media or charging legally in courts with evidence blaming INSA of commiting a crime . Never backed up by evidence. It is just rumor fake news .

    Not Abebe or any other person ever came forward stating dates and events when INSA silenced or harmed any Ethiopian while Dr. Abiy was leading the agency.
    No proof or evidence was never seen till.this day. So it is just a campaign politically motivated stunt.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.