ለቸኮለ! የዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 10/2013 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክር ቤት የከተማዋን ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች እንደገና ለማደራጀት የቀረበለትን የማሻሻያ አዋጅ እነዳጸደቀ አዲስ ቲቪ ዘግቧል፡፡ በአዲሱ አደረጃጀት ከቦሌ እና የካ ክፍለ ከተሞች የተወሰኑ ወረዳዎች ተወስደው ለሚ ኩራ የተሰኘ አዲስ ክፍለ ከተማ እንዲቋቋም ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡ የአደረጃጀት ማሻሻየው መጽደቁ፣ የከተማዋን ክፍለ ከተሞች ብዛት ወደ 11 ከፍ አድርጎታል፡፡ ምክር ቤቱ የአዳዲ ሃላፊዎችን ሹመትም አጽድቋል፡፡
2. የሀገሪቱ የምርጫ ሥርዓት እንዲቀየር ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያነሱት ሃሳብ ላይ ጥናት ማድረጉን ምርጫ ቦርድ ዛሬ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡ አዲስ ማሻሻያ ይደረግ ከተባለ፣ የአብላጫ ድምጽ እና የተመጣጣኝ ውክልና ምርጫ ሥርዓት ድቅል የሆነው ቅይጥ የምርጫ ሥርዓት ይሆናል ብሎ እንደሚገምት ቦርዱ ጠቅሷል፡፡ የጥናቱ ዐለማ የምርጫ ሥርዓትን መቀየር በምርጫው፣ በሕግ እና ቴከኒክ ረገድ ምን አንድምታዎች እንዳሉት መጠቆም እንደሆነ ቦርዱ ገልጧል፡፡ ምርጫ በሚካሄድበት ዐመት የምርጫ ሥርዓትን ማሻሻል ወይም መለወጥ በምርጫው ሂደት ተዓማኒነት እና ተቀባይነት ላይ ከፍተኛ ደጋ ይደቅናል ይላል የቦርዱ ጥናት፡፡
3. ከጎንደር እና ባሕር ዳር ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ ሹፌሮች ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚደርስባቸው ጥቃት ሳቢያ ሥራ መስራት እንዳልቻሉ ለኢቢሲ ተናግረዋል፡፡ ስለደረሰባቸው ጥቃት ቃላቸውን የሰጡት መስከረም 30 ሌሊት የክልሉን ልዩ ሃይል ደንብ ልብስ የለበሱ ታጣቂዎች ገብረ ጉራቻ ከተማ አቅራቢያ ተኩስ ከፍተው ያቆሰሏቸው የጭነት መኪና ሹፌሮች ናቸው፡፡ የክልሉ ፓሊስ ኮሚሽን ጥቃቱ ሹፌሮቹ ላይ እንደተፈጸመ አምኖ፣ ድርጊቱን የፈጸሙት ግን በተለያየ ምክንያት ከክልሉ ጸጥታ ሃይል ከድተው ጸረ ሰላም ሃይሎችን የተቀላቀሉ ሕገወጥ ታጣቂዎች እንጅ የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት አይደሉም ሲል አስተባብሏል፡፡
4. የቻይና ሲቪሎ አቬሽን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሻንጋይ በሚያደርገው በረራ ላይ ከመጭው ሰኞ ጀምሮ የ5 ሳምንታት እገዳ እንደጣለ ሻይን የተሰኘው ድረገጽ ዘግቧል፡፡ ዕገዳው የተጣለው በዚህ ወር ከአዲስ አበባ ወደ ሻንጋይ ከተደረጉ ሁለት በረራዎች 16 መንገደኞች ላይ ኮሮና ቫይረስ ስለተገኘባቸው ነው፡፡ ካንድ አየር መንገድ ባድ በረራ በቫይረሱ የተያዙ 5 እና ከዚያ በላይ መንገደኞች ከተገኙ፣ ሲቪል አቬሽኑ የበረራ እገዳዎችን ይጥላል፡፡
5. መከላከያ ሠራዊት ሁለት አዳዲስ ወታደራዊ ዕዞችን ሊያደራጅ እንደሆነ ፋና ብሮድካስት ዘግቧል፡፡ አዲሶቹ ዕዞች በሰሜን ምዕራብ እና ማዕከላዊ ዕዦች ስሆኑ፣ መቀመጫቸው ባሕር ዳር እና አዲስ አበባ ላይ ይሆናል፡፡ ዕዞቹ እንዲቋቋሙ የተወሰነው፣ በሀገሪቱ ውስጣዊ እና ውጫዊ የብሄራዊ ደኅንነት ስጋቶች ላይ ጥናት ከተደረገ በኋላ መሆኑን የጦር ሠራዊቱ ኤታማዦር ሹም አደም መሐመድ እና ምክትላቸው ትናንት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡ የሁለቱ ዕዞች መቋቋም የሠራዊቱን ዕዞች ስድስት ያደርሳቸዋል፡፡
6. ጨረታ አሸንፈው በቴሌኮም አገልግሎት የሚሠማሩ የውጭ ቴሌኮም ኩባንያዎች በ5 ዐመት ውስጥ 98 በመቶ ለሚሆነው ሕዝብ የድምጽ እና ጽሁፍ መልዕክት አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው የሚያዝ መመሪያ እንደተረቀቀ ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ አገልግሎት ሰጭ ኩባንያዎች ባንድ ዐመት ውስጥ አገልግሎታቸውን በሁሉም ዞኖች እና ወረዳዎች ተደራሽ ማድረግ አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኮምንኬሽን ባለሥልጣን ያዘጋጀው የሕግ ማዕቀፍ ኩባንያዎቹ ማቅረብ ያለባቸውን የኢንተርኔት ጉልበት ወለልም ወስኗል፡፡
7. የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት እና የመን በበረሃ አንበጣ ወረራ ሳቢያ በተያዘው የፈረንጆች ዐመት 8.5 ቢሊዮን ዶላር ሊያጡ እንደሚችሉ የዐለም እርሻ ድርጅትን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ከጥር ጀምሮ በኢትዮጵያ ብቻ አንበጣው 200 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያሉ እጽዕዋትን እንዳወደመ ድርጅቱ ገልጧል፡፡ አንበጣው በምሥራቅ አፍሪካ ትልቅ ጉዳት እየደረሰ ያለው ኢትዮጵያ ላይ ነው፡፡ የአንበጣ መንጋው ወረራ በቀጣዩ የፈረንጆች ዐመትም ሊደገም እንደሚችል በኢትዮጵያ የድርጅቱ ሃላፊ አስጠንቅቀዋል፡፡
8. የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሱዳንን ከአሸባሪነት ዝርዝር እንደሚፍቁ ተናንት በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡ ሱዳን ከአሸባሪነት ዝርዝር የምትፋቀው ግን ከ20 ዐመታት በፊት ናይሮቢ እና ዳሬሰላም በሚገኙ የአሜሪካ ኢምባሲዎች ላይ በተፈጸሙ የሽብር ጥቃቶች ለሞቱ ሰዎች ለመክፈል የተስማማችውን የ335 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ገቢ ስታደርግ እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡ ሱዳን ከአሜሪካው የአሸባሪነት መዝገብ ከተሰረዘች፣ ከዐለማቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች ብድር እና የብድር ስረዛ እንዲሁም የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ ትችላለች፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.