የክራይሲስ ግሩፕ አጥኚ ዊሊያም ዳቪሰን በቅርቡ በመቀለ በነበረው ቆይታ ምን አስተዋለ?

የዓለም አቀፉ ክራይሲስ ግሩፕ ከፍተኛ አጥኚ ዊሊያም ዳቪሰን በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ክልል መካከል ያለው ውዝግብ ለመገምገም ወደ መቀለ ከተጓዘ በኋላ ለድርድር ፍላጎት እንዳለ የሚያሳይ ነገር የለም ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።

በአይሲጂ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ከፍተኛ አጥኚ የሆነው ዊሊያም ዳቪሰን፤ ከሰሞኑ ወደ መቀለ ያቀናው ክልሉ ከፌደራል መንግሥት ጋር ስለገባበት ውዝግብ ያለውን አቋም ለመገምገም እና ከገቡበት አጣብቂኝ የሚወጡበትን መፍትሄው ለማፈላለግ መሆኑን ይናገራል።

በመቀለ ቆይታውም የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ከበርካታ የክልሉ ኃላፊዎች ጋር መነጋገሩን የሚያስረዳው አጥኚው፤ በቆይታው ለድርድር ፍላጎት መኖሩን የሚያሳይ ነገር የለም ብሏል።

ከሁለት ወራት በፊት ዓለም አቀፉ ክራይሲስ ግሩፕ (አይሲጂ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ አስታራቂና የሚያቀራርቡ ንግግሮቻቸውን ወደ ተግባር እንዲለውጧቸው መጠየቁ ይታወሳል።

አይሲጂ ጨምሮም በሁለቱ አካላት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ አስፈላጊ ከሆነም የአፍሪካ ሕብረት ወይም የአፍሪካ መሪዎች በማሸማገሉ በኩል ተሳትፎ ሊያደርጉ ይችላሉ ከማለት በተጨማሪ በተለይ የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር የሆኑት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ ብሏል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ከትግራይ ክልል ጋር የተከሰተው አለመግባባት “በሕግ እና ሕግ ብቻ የሚመለሰው ይሆናል” ያሉ ሲሆን የፌዴሬሽን እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚሰጡት ውሳኔ ላይ ብቻ በመመሠረት ጉዳዩ በሕግ የሚመለስ መሆኑን ተናግረዋል።

የአይሲጂ አጥኚ ዊሊያም ዳቪሰን “በክልሉ እና በፌደራል መንግሥት መካከል ያለው ፍጥጫ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው። በፓርቲዎቹ መካከል ያለው ትስስር እየቀነሰ ነው። የፌደራል መንግሥት የትግራይን በጀት ካቋረጠ ነገሮች ሊባባሱም ይችላሉ” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ዊሊያም ጨምሮም፤ የፌደራል መንግሥት ለትግራይ ክልል የሚሰጠውን በጀት ካቋረጠ “ክልሉ ይህንን እንደ ጦርነት ትንኮሳ እና ከፌደሬሽኑ እንደመገፋት አየዋለሁ ብሏል። ይሄም አሳሳቢ ነው” ሲል ተናግሯል።

ዊሊያም “ሁለቱም ወገኖች ወደ ጠረጴዛው መጥተው የሚወያዩበት መንገድ ማግኘት አለባቸው። ይህ ካልሆነ ቀውስ ይከተላል” ብሏል።

“በኢትጵያ ያሉ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች መወያየት ይፈልጋሉ ብዬ አስባለሁ። ብልጽግና ፓርቲ፣ የኦሮሞ፣ የሶማሌ፣ በደቡብ የሚገኙ ፓርቲዎች፣ ሕወሓትና የትግራይ ተቃዋሚዎችም መወያየት ይፈልጋሉ። ችግሩ ግን ምን አይነት ድርድር ማድረግ እንዳለባቸው፣ ግባቸው ምን እንደሚሆን፣ ቅድመ ሁኔታዎቹ ምን መሆን እንዳለባቸው የተለያየ አመለካከት ነው ያላቸው። ይህም ፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ መድረክ መጥተው ውይይት እንዳያደርጉ እክል ይሆናል” ይላል።

በትግራይ በነበረው ቆይታ የተረዳውንም ሲያስረዳ፣ የትግራይ ክልል መንግሥት ወደ መሰል ድርድር ወይም ውይይት ሊገባ የሚችለው ጠንከር ያሉ ቅድመ ሁኔታዎች ሲጠበቁ ነው።

“ለምሳሌ ምርጫውን የሚመራ ባለአደራ መንግሥት ይቋቋም የሚል ነጥብን አላቸው። አሁን ላይ የፌደራል መንግሥቱ ወይም ገዢ ፓርቲው ይህን ቅድመ ሁኔታ የሚቀበልበት ሁኔታ ያለ አይመስልም።”

ዊሊያም በጉዳዩ ላይ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ጋር ተገናኝቶ የመነጋገር ፍላጎት ቢኖረውም እድሉ ግን እስካሁን እንዳልተመቻቸ ይናገራል።

የክራይሲስ ግሩፕ ከፍተኛ አጥኚ የሆነው ዊሊያም ዳቪሰን፣ ድርጅታቸው አሸማጋይ አለመሆኑን ይናገራል። “ሁለቱንም አካሎች የምናነጋግረው ግንዛቤያችንን ለማዳበር ነው። ትንታኔያችን የሁሉንም አካላት አስተያየት የያዘ እንዲሆን የተሟላ ጥናት እየሠራን ነው። ከዛ ምክረ ሐሳባችን ለሁሉም አካል ትርጉም የሚሰጥ ይሆናል” ብሏል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የትግራይ ክልልን በሚያስተዳድረው ሕውሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል አለመግባባቶች እየተካረሩ መጥተዋል።

ባለፈው ዓመት ለማካሄድ ታስቦ የነበረው አገራዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ስርጭት ስጋት እንዲራዘም ተደርጎ የትግራይ ክልል የራሱን ክልላዊ ምርጫ ማከናወኑ በሁለቱ አካላት መካከል ያለውን ውጥረት ከፍ አድርጎታል።

BBC

1 thought on “የክራይሲስ ግሩፕ አጥኚ ዊሊያም ዳቪሰን በቅርቡ በመቀለ በነበረው ቆይታ ምን አስተዋለ?

  1. ሲጀመር እዛ ምን ያደርጋል? እነርሱ አይደል እንዴ በየምክንያቱ ነገርን በነገር እየሳሉ ዛሬ በዓለም ዙሪያ ሰው እንዲፋለስ የሚያድርጉት? የሚያሳዝነው ነገር ጥቁሩ ህዝብ የራሱን ገመና ለነጭ ማሳየት ይቀለዋል ከጎኑ ካለው ወገኑ ጋር ተደራድሮ ነገርን ከመፍታት ይልቅ። በመሰረቱ ወያኔ ትግራይ ላይ መሽጎ አሻፈረኝ ማለቱ ያው በ 27 አመቱ የመከራ ዘመን በራሱ አስቦና ለራሱ ሃብት ዘርፎ የኖረበት ጊዜ ናፍቆት እንጂ ለትግራይ ህዝብ ድሮም ሆነ ዛሬ ገዶት አያውቅም። ታሪኩን መመርመር በቂ ነው። የሚያሳዝነው ግን በጠ/ሚሩና በወያኔ የጦር አበጋዞች መካከል በሚደረገው ሽኩቻ የሚጎዳው ያው መከረኛ የትግራይ ህዝብ ነው። እንዲያ እኮ ነው የነበረው ያኔም ደርግ በዚህ ሲያስርና ሲገድል፤ በሰፈራ ሂሳብ ህዝብን ሲያመሳቅል ወያኔ ደግሞ ተመሳሳይ ግፍ በትግራይ ህዝብ ይፈጽም ነበር። ታዲያ የሰውና የአለም መሳለቂያ ከመሆን ወያኔ ራሱን ለውጦ በሃሳብ ፍትጊያ ጠ/ሚሩን ረትቶ ህዝባችን በሰላም እንዲኖር ከማድረግ ይልቅ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ጅልነት ነው። እልፍ ወታደር ቢሰለፍ በአሁኑ የጦርና የውጊያ ስልት አንድ ሃያል ሃገር እንካችሁ ብሎ ለአንደኛው ወገን ትጥቅና ስንቅ ካቀበለ ዝም ብሎ መተላለቅ እንጂ አሸናፊና ተሸናፊ አይኖርም። ቀረርቶው፤ ልዪ ስልጠናው፤ በአየርና በምድር መርመስመሱ ዋጋ ቢስ ነው። ሰላም የሁሉ መሰረት ነው። ጦርነት የኋላ ቀርነትና የመከራ ምንጭ ነው። የትግራይ ህዝብ ሃበሳና መከራ መቼ ነው የሚያቆመው? የፈለገውን መርጦ፤ በራሱ አስቦና ጽፎ የሚኖረው መቼ ነው? በወያኔ ሳንባ ተንፍሶ በወያኔ ጭንቅላት አስቦ እስከ መቼ መኖር ይችላል? ዋ ነግሬአለሁ እናንተ የሃገር እብሪተኞች ሰከን በሉ። የጣሊያኑ ሞሶሎኒ ከጀርመኑ ሂትለር ጋር አብሮ የሃበሻዋን ምድርና አልቤኒያን ሲወር ዓለም በዝምታ አየው። የተከለከለ መርዝ ማንበብና መጻፍ በማያውቅ ህዝብ ላይ ሲረጭ የተቃወመ የለም። ግን የሞሶሎኒን ፍጻሜ ላዬ ወዮ አታድርስ ያሰኛል። ሮም ላይ ተዘቅዝቆ ነው የተሰቀለው። የወያኔ ግፈኞችም ሆኑ አሁን እነርሱን የተኩት የኦሮሞ ጽንፈኞች ዋ ያ ቀን ይመጣል ልብ በሉ የሰው እንባ የሰው ደም ተሟጋች አለው። ባጭሩ ነጭም ሆነ አረብ ሃገር ገብቶ ይህን ሰማሁ ይህን አየሁ ማለቱ ለሃገርም ለህዝባችንም ጠቃሚነት የለውም። ሌላ ተልዕኮ ይዘው ነውና ወደ ሃገር የሚገቡት። በራስ አስቦና በራስ ተማምኖ ሰላምን በወገኖች መካከል አስፍኖ ለሥራ የተነሱ እጆችን እንጂ ሌላው ቆሻሻ ነው ብሎ ሊጥለው የነበረውን መሳሪያ ተሸክሞ ወገንን መግደልና ማስፈራራት የድንጋይ ዘመን አስተሳሰብ ነው። ስለሆነም ወያኔዎችና የብልጽግና (የድህነት) ፓርቲ ተነጋገሩና ችግራችሁን ፈታችሁ ለሃገሪቱና ለህዝባችን ሰላም ስጡ። ሌላው ሁሉ አሸሸ ገዳሜ ሃላፊ ነውና የወገን ምክር ስሙ! በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.