በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ በማይገኙ የትግራይ ክልል ተወካዮች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ይወሰዳል – አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11 ፣2013 (ኤፍ.ቢ. ሲ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በማይገኙ የትግራይ ህዝብ የወከላቸው የምክር ቤቱ አባላት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ተናገሩ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው ባለፉት ሁለት የምክር ቤቱ ስብሰባዎች ላይ ከአንድ ተወካይ በስተቀር ከትግራይ ክልል የተወከሉ የምክር ቤት አባላት አለመገኘታቸውን አስታውቀዋል።
በምክር ቤቱ በኩል ተወካዮቹ እንዲገኙ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰው÷ ባለመገኘታቸው የሚቀጥሉ ከሆነ ግን አስተዳደራዊ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
አፈ-ጉባኤው በመግለጫቸው እንዳሉት ማንኛውንም ችግር በውይይት፣ በህግና አሰራር መፍታት እንጅ ሃገርን የማፍረስና ህግን የመተላለፍ ተግባር መፈጸም እንደሌለበት አስረድተዋል።
ዘንድሮ የሚካሄደውን ምርጫ በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከ90 በመቶ በላይ የምርጫ ቁሳቁስ አቅርቦቱ እንዳጠናቀቀ መረጋገጡን ጠቅሰዋል።
በምርጫ ሂደቱ ለሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል የውድድር ሜዳ እንዲፈጠር መሰራት እንዳለበት መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ምርጫው ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ የሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጁነት ወሳኝ መሆኑንም ነው የገለጹት።
ምክር ቤቱ ወደ ህዝቡ ይበልጥ በመቅረብ እየሰራ ነው ያሉት አፈ-ጉባኤው÷ በጎርፍ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች በገንዘብና ቁሳቁስ 40 ሚሊየን ብር መለገሱን አስታውሰዋል።
በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ መንጋ የሚገመግም የምክር ቤት አባላት ልዑክ ወደ ተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች መንቀሳቀሱንም ገልጸዋል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.