ለቸኮለ! የዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 12/2013 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. በደቡብ ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ በታጣቂዎች የተገደሉት ንጹሃን ዜጎች ቁጥር ወደ 31 እንዳሻቀበ ፋና ብሮድካስት ዘግቧል፡፡ ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ አንድ ፖሊስ እና የመንግሥት ሃላፊዎችን ጨምሮ 16 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ በጥቃቱ ሌሎች 5 ሰዎች ቆስለዋል፡፤ ከ1 ሺህ 400 በላይ ነዋሪዎች ደሞ ተፈናቅለዋል፡፡ ባለፈው ዕሁድ ከተፈጸመው ጥቃት በተጨማሪ፣ ሌላ ጥቃት ትናንት ተፈጽሟል፡፡ ጥቃቱ በሁለት ቀበሌዎች ውስጥ በሚኖሩ አርሶ አደሮች ላይ የተፈጸመው በሁለት የተለያዩ ቀናት ነው፡፡
2. የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ለከፍተኛ ኪሳራ የዳረጉ የቀድሞ እና የአሁን አመራሮች ላይ ክስ እንዲመሠረትባቸው የተዘጋጀው ሰነድ ተድበስብሶ እንዲቀር መደረጉን ዋዜማ ከምንጮቿ መረዳት ችላለች፡፡ ልማት ባንክ እስከ 20 ቢሊየን ብር የሚደርስ የተበላሸ ብድር የተከማቸበት ተጠያቂነት በሌለበት ብድር አሰጣጥ ሳቢያ እንደሆነ ሰነዱ ያብራራል፡፡ ሰነዱ 80 ተበዳሪዎችን፣ በብድሩ አሰጣጡ ጊዜ የታዩ የሕግ ጥሰቶችን፣ ውሳኔ ሰጭ አመራሮችን እና ሙያተኞችን ስም ዝርዝር እና ሚናቸውን አካቷል፡፡ Link- https://bit.ly/31uUhc6
3. በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ ዐቃቤ ሕግ በእነ እስክንድር ነጋ ጉዳይ ምስክሮች በዝግ ችሎት እና ከመጋረጃ በስተጀርባ እንዲሰሙለት ያቀረበው አቤቱታ ከፍታኛ ተቃውሞ እና ክርክር እንዳስነሳ ዋዜማ ሰምታለች፡፡ ምስክሮቹ ከተከሳሾች ጋር ጥብቅ ግንኙነት ስላላቸው ለበቀል ጥቃት ይጋለጣሉ፤ በቀዳሚ ምርምራ ምስክር ማሰማት ሂደት ላይም የግድያ ዛቻ ደርሶባቸዋል በማለት መከራከሪያ አቅርቧል ዐቃቤ ሕግ፡፡ ተከሳሽ እስክንድር በበኩሉ ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ከተቀበለ መገናኛ ብዙኀን የምስክሮችን ዝርዝር ቃል እንዳይገልጹ የተጣለባቸው ገደብ ተነስቶላቸው ሂደቱን እንዲከታተሉ ጠይቋል፡፡
4. ዐለማቀፍ ለጋሽ ሀገሮች ለትግራይ ገበሬዎች ሲሰጡት የቆዩትን የሴፍቲኔት ዕርዳታ ፌደራል መንግሥቱ እንደከለከለ የክልሉን ግብርና እና ገጠር ልማት ቢሮ ጠቅሶ ሕወሃት በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡ ለጋሾች ለዘንድሮው የሴፍቲኔት መርሃ ግብር የሰጡትን የገንዘብ ዕርዳታ ፌደራል መንግሥቱ ጥቅምት 10 ለክልሎች ያከፋፈለ ሲሆን፣ ለትግራይ ገበሬዎች የተመደበውን የሁለት ወር በጀት ማለትም 285 ሚሊዮን ብር ግን አስቀርቷል፡፡
5. አዲስ ተረቅቆ ከሁለት ሳምንት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የወንጀለኛ መቅጫ ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር እንደጠየቀ ሪፖርተር አስነብቧል፡፡ ማኅበሩ ጥያቄውን ያቀረበው በረቂቁ ውስጥ መሻሻል፣ መስተካከል እና አዲስ መካተት ያለባቸው ነጥቦች በመኖራቸው እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ረቂቁ ስለ ሕግ ጠበቆች ምንም ያለው አለመኖሩን ማኅበሩ እንደ አንድ ጉድለት ጠቅሷል፡፡
6. የሙስና ክስ የተመሠረተባቸው የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የቀድሞው ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ 8 ተከሳሾች የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ እንደሰጠ ፋና ብሮድካስት ዘግቧል፡፡ ተከሳሾቹ መከላከያ ማስረጃቸውን ለዛሬ እንዲያቀርቡ ችሎቱ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ ዛሬ ባለማቅረባቸው ከጥር 24 እስከ 28 ቀን የእንዲያቀርቡ ታዘዋል፡፡ ዐቃቤ ሕግ አምና ምስክሮቹን አሰምቶ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
7. ዐለማቀፉ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን በሰብዓዊነት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች እንዲከሰሱ ለስዊድን ዐቃቤ ሕግ የክስ ሰነድ እንዳቀረበ በድረገጹ አስታውቋል፡፡ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ በተጨማሪ፣ የውጭ ጉዳይ፣ ፍትኅ እና ማስታወቂያ ሚንስትሮች በክሱ እንዲካተቱለት ጠይቋል ድርጅቱ፡፡ የክሱ ጭብጥ ለ2 አስርት ዐመታት በኤርትራ እስር ላይ ያለው ኤርትራዊ-ስዊድናዊ ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ ነው፡፡ ስዊድን በባለሥልጣናቱ ላይ ጠንከር ያለ ምርመራ እንድትከፍት የጠየቀው ድርጅቱ፣ ጋዜጠኛውን በማገት፣ በመግረፍ እና ደብዛውን በማጥፋት ክስ ይመሰረትባቸዋል ብሎ እንደሚጠበቅ በድረ ገጹ ገልጧል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.