በኬንያ ፖሊስ ተይዘው ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፈው ሊሰጡ ነበር የተባሉ በህዝብ አቤቱታ ተለቀቁ – ዳዊት ሰለሞን

የኢትዮጵያ መንግስት ያሰማራቸው ሰላዮች በህዝብ ጥቆማ ቢያዙም መለቀቃቸው ህዝቡን አስቆጥቷል
10ትናንት ረፋድ አካባቢ በናይሮቢ ነዋሪ የሆኑ ሶስት የፖለቲካ ስደተኛ ኢትዮጵያዊያን በኬንያ ፖሊስ ለጥያቄ እንደሚፈለጉ ተነግሯቸው ሲወሰዱ በዛ ያሉ ሰዎች ተፈላጊዎቹን በመከተል ፖሊስ ጣብያ ድረስ በማምራት የተያዙት እንዲለቀቁ አልያም ተላልፈው ለኢትዮጰያ መንግስት እንዳይሰጡ በመጠየቅ ምላሽ ካላገኙ ፖሊስ ጣብያውን እንደማይለቁ በማስረዳታቸው የፖሊስ ጣብያው ኃላፊዎች ሰዎቹን አሳልፈው እንደማይሰጡ ቃል በመግባት በነጋታው መጥተው እንዲያናግሯቸው አስረድተዋቸው ሰዎቹ ወደ መኖሪያቸው ተመልሰው ነበር፡፡
ዛሬ ማለዳ ፖሊስ ጣብያው ድረስ በመትመም ታሳሪዎቹ ለምን እንደታሰሩና የኬንያ ፖሊስ ከኢትዮጵያ አቻው ጋር በመተባበር በስደተኞቸ ላይ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ የጠየቁት በመቶዎች የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡በህዝቡ ብዛት የተገረሙት የፖሊስ መምሪያው ኃላፊዎች ኮሚቴ መርጣችሁ አናግሩን ቢሉም ህዝቡ አንድ ቃል በማውጣት‹‹የታሰሩት ኮሚቴዎቻችን ነበሩ፡፡እነርሱ ታስረውና ህይወታቸው አደጋ ላይ ወድቆ ሌላ ኮሚቴ አንመርጥም፡፡ካናገራችሁን ሁለችንንም አናግሩን ካልሆነም ሁላችንንም እሰሩን በማለታቸው ፖሊሶቹ አማራጭ በማጣት የታሰሩትን ሶስት ሰዎች ለመፍታት በቅተዋል፡፡
ህዝቡ ከፖሊስ መምሪያው ሃላፊዎች ጋር ባደረገው ውይይት በኬንያ ፖሊስ ድርጊት እያዘነ መምጣቱንም ከመግለጽ አልተቆጠበም‹‹ለምሳሌ በያዝነው ሳምንት የኢትዮጵያ መንግስት ያሰማራቸውን በስደተኛ ስም የሚንቀሳቀሱ ሰላዩች ከተለያዩ ቁሳቁሶች ጋር በመያዝ አሳልፈን የሰጠናችሁ ቢሆንም ፍርድ ቤት ሳታቀርቧቸው ለቅቃችኋቸዋል፡፡ሰዎቹ በዋስ እንደወጡና በቀጣዩ ሳምንት ፍርድ ቤት እንደምታቀርቧቸው ብትነግሩንም ይህ እንደሚሆን እርግጠኛ መሆን አንችልም››ብለዋል፡፡
ህዝቡ አሳልፎ ለፖሊስ የሰጣቸውና ለኢትዮጵያ መንግስት ይሰልሉ እንደነበር ከተነገረባቸው ሰዎች መካከል በአንዱ እጅ ሶስት የእጅ ስልኮች፣ፖሊሶች የሚይዙት መገናኛ(ዎኪ ቶኪ)እንዲሁም በአንደኛው ተጠርጣሪ መኖሪያ ቤት ውስጥ ከሰባ የሚልቁ ስደተኛ ኢትዮጵያዊያን ስምና ብዛት ያላቸው ፎቶ ግራፎች መገኘታቸውን በወቅቱ ካነጋገርኳቸው ሰዎች ለመረዳት ችያለሁ፡፡
ኢንጂነር ተስፋሁን ጨመዳ ከኬንያ ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ በኢትዮጵያ በተደረገበት መሰቃየት ለሞት መዳረጉን በምሬት የሚያስታውሱት ስደተኞቹ ‹‹ በኬንያ ባልታወቁ ሰዎች ተገድለው የሚገኙ ወገኖቻችንና ከዚህ ታፍነው እየተወሰዱ በኢትዮጵያ እስር ቤቶች በመሰቃየት ላይ ስለሚገኙ ሁሉ ፍትህን ከመጠየቅ ለአፍታ አናመነታም፡፡ብለዋል፡፡
በኬንያ ከ37000 የሚልቁ ስደተኛ ኢትዮጵያዊያን እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቀማሉ፡፡

Netsanet Beqalu Mannet's photo.Netsanet Beqalu Mannet's photo.
ዳዊት ሰለሞን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.