“ታደለ ዛሬም ታድሏል!” – ከኤርሚያስ ለገሰ (የመለስ ትሩፋቶች መጽሐፍ ደራሲ)

ምርጫ 2007 እንዲታዘቡ ከተፈቀደላቸው ተቋማት አንደኛው የኢትዬጲያ ሲቪክ አደረጃጀቶችን እንዳቀፈ የተነገረለት ” ጥምረት” ነው። ይህ ጥምረት የወጣቶችና ሴቶች ማህበራት፣ ፎረምና ፌዴሬሽን እንዲሁም የተለያዩ የሙያ አደረጃጀቶችን ይዟል በሚል የገለልተኛነት ስያሜ ተሰጥቶት የተቋቋመ ነው። ይሁን እንጂ ወደ ውስጥ ጠለቅ ብሎ ለተመለከተው ጥምረቱ ከትግራይ በፈለቀው ገዥ መደብ የተደራጀ አንዱ ” የኢህአዴግ ክንፍ” ነው። ተጠሪነቱም ላደራጀው አካል ነውና ግብሩም ተመሳሳይ መሆኑ አይቀርም። ስለዚህም ምርጫው በተካሄደ በማግስቱ ባወጣው መግለጫ ” ምርጫው ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ነጳ ነበር” እንዳለ ሰምተናል። ይህ የጥምረቱ አባባል የሚጠበቅ ስለሆነ በሰፊው መነጋገሪያ መሆን አልቻለም። በእኔ እምነት ይህን በንቀት ማለፋ ተገቢ መስሎ አልታየኝም። በተለያዩ ምክንያቶች። በመጀመሪያ ደረጃ ህውሀትም ሆነ ምርጫ ቦርድ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በሚያዘጋጇቸው ሰነዶች የምርጫውን ነጳና ፍትሀዊነት ለማሳየት ከሚጠቀሙባቸው ማስረጃዎች ዋነኛው የጥምረቱን ሪፓርት እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው። በተለይም አደረጃጀትን ከላይ ከላይ በማየት ይሁንታ ለመስጠት ለሚሞክሩ የውጭ ሀይሎች የጥምረቱን ምንነት ማስረዳት ካልተቻለ አሉታዊ ሁኔታዎች ሊፈጥር ይችላል። ከልምድ እንደሚታወቀው የውጭ ሀገር በተለይም የምእራቡ አለም ሰዎች በሲቪክ አደረጃጀቶች ነጳነት ላይ ብዙ ጥያቄ ሲያነሱ አይታይም። ይህን ድክመታቸውን ህውሀት ጠንቅቆ ያውቀዋል። ይህንንም ለማሳየት በተለያዩ የባእድ ሀገር ቋንቋዎች መጣጥፎችን አዘጋጅቶ በሰፊው የማሰራጨት ስራ ይሰራል።

በመሆኑም ከትግራይ የፈለቀው ገዥ መደብ ጥምረቱን አስመልክቶ ምን አይነት ግምገማ ያስቀምጣል የሚለውን አስቀድሞ መገመቱ ተገቢ ይሆናል። የሚጵፈውን ግምገማና ሪፓርት በምን መልኩ እና በማን ያስተላልፋል የሚለውንም አብሮ መመልከት ያስፈልጋል። አሁንም ከቀድሞ ሪፓርቶችና ልምድ በመነሳት ገዥ መደቡ ስለ ጥምረቱ የሚከተለውን ይጵፋል ተብሎ ይገመታል፣

” …ዜጐች በነጳ ፍቃዳቸው በተደራጁበት አደረጃጀታቸው በምርጫ ታዛቢነት የሚሳተፋት የአገሪቱ ዜጐች በመሆናቸው ብቻ ማንም ሊሰጣቸውና ሊከለክላቸው የማይችል በህገመንግስታችን የተከበረላቸው የማይገረሰስ መብት ስላላቸው ነው። ይህም የአገራችን እጣ ፋንታና ሉአላዊነት በዜጐችና ዜጐች ብቻ የሚወሰን መሆኑን ያመላክታል። በመሆኑም የዜጐች አደረጃጀት የሆነው ‘የሲቪክ ማህበራት ጥምረት ‘ ምርጫውን በነጳነት ለመታዘብ ህብረት ሲፈጥሩ መንግስት በደስታ ተቀብሎታል። ይህም በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ሉአላዊነትንን ለዜጐች እንጂ ለውጭ ሀይሎች አሳልፎ የማይሰጥ መሆኑን አመላካች ነው። በዚህ የፀና አቋም በመነሳት ጥምረቱ በመላ ሀገሪቱ ተዘዋውሮ በነጳነት እንዲታዘብ ተደርጓል። የትዝብት ሪፓርቱንም ያለአንዳች ጫና ለመላው የሀገራችን ህዝቦች ይፋ አድርጓል። የጥምረቱ ሪፓርት የ2007 ምርጫን እንከን የለሽ ፣ ነጳና ፍትሀዊ እንደሆነ በማያሻማ መንገድ አብስሯል። ይህም ለሀገር ውስጥ ቀለም አብዬት ናፋቂዎችና ፀረ-ህዝቦች ግልጵ መልእክት እንዲደርሳቸው አድርጓል ። የጥምረቱ ሪፓርት ለሀገራችን የጥፋት ሀይሎች ብቻ ሳይሆን አዲስ የቀኝ ግዛት አስተሳሰብ ለተጣባቸው እንደ አውሮፓ ህብረት ላሉ ፍጥረቶች የሀገራችን ዲሞክራሲ በኢትዬጲያውያን ብቻ የሚወሰን መሆኑን አሳይቷል” የሚል ይዘት ያለው ዳጐስ ያለ ዶክመንት ያለጥርጥር ያወጣል። በኤክትሮኒክስ ሚዲያና ወርሀዊ ቀለብ በሚቆርጥላቸው እንደ አይጋ ፎረም፣ ትግራይ ኦን ላየን፣ ኢትዬጲያን ፈርስት( ” ሚስተር ቤን!!”) የመሳሰሉ የሚዲያ ተቋማት እንዲሰራጭ ያደርጋል።

በመሆኑም ከወዲሁ ፕሮፐጋንዳውን ሊያረክሱ የሚችሉ ነጥቦችን በመለየት አስቀድሞ ምላሽ ማዘጋጀት ተገቢ ይሆናል። የዛሬው መነሻችን ” የሲቪክ አደረጃጀቶች ጥምረት” ነውና በዚህ ዙሪያ የምናውቀውን፣ የታዘብነውንና በአይናችን የተመለከተውን በማንሳት ገዥው መደብ ከእውነቱ ጋር እንዲጋፈጥ ማድረግ ከሁላችንም ይጠበቃል። በዚህ ዙሪያ ሁሉም ሊሳተፍ ይችላል። ይገባልም። ለምሳሌ ጥምረቱን ወክለው በምርጫ ታዛቢነት የተሳተፋትን ግለሰቦች ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን ከጀርባ ማጥናትና በስም ዝርዝር ማጋለጥ። በማህበራዊ ድህረ ገጵም በተቻለ መጠን በፎቶ አስደግፎ ” የህዝብ ድምጵ ሰራቂዎች” በሚል ርእስ እንዲወጡ ማድረግ።

በነገራችን ላይ ሁሉም የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ አባላት ከተጣለባቸው ግለሰባዊ ተልእኮ ዋነኛው በማህበር፣ በፎረምና ፌዴሬሽን አባልነት በግዴታ መሳተፍ ነው። ይህን ያላደረገ ተግባር እንዳንጠባጠበ ተቆጥሮ ድርጅታዊ ቅጣት ይጣልበታል። በመሆኑም አንድ የኢህአዴግ አባል አንድም፣ ሶስትም፣ አራትም ነው። በሌላ አነጋገር አንድ ” ማንከልክሎሽ” የምትባል እህታችን የሴት ሊግ አባል ብትሆን እዛው ሳለች የፎረምና ፌዴሬሽን አባል ትሆናለች። ስራዋ ጥቃቅን ከሆነም በጥቃቅን አደረጃጀት ትታቀፋለች።( በሂሳቢኛ: ሴት ማህበር + ሴት ፎረም + ሴት ፌዴሬሽን + ጥቃቅን <= የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ)…በተመሳሳይ መንገድ ” አባዲ” የሚባል ታናሽ ወንድማችን የወጣት ሊግ፣ ማህበር፣ ፎረምና ፌዴሬሽን አባልና አመራር አቀናጅቶ ይይዛል። የአባዲ ስራ “መሬት ድለላ” ከሆነ ደግሞ እዛው ሳለ የደላሎች ማህበር አመራር ይሆናል።( ወጣት ማህበር + ወጣት ፎረም + ወጣት ፌዴሬሽን + ወጣት ደላላ +… …<= የኢህአዴግ ወጣት ሊግ)!!

እንግዲህ ጥምረቱ በህውሀት ተቋቁሞ እንደ አንድ የኢህአዴግ ክንፍ የሚያገለግል መሆኑን ከተስማማን በግለሰብ ደረጃ የጥምረቱ አመራሮች እነማን ናቸው የሚለውን መመልከቱ ቀጣይ ስራ ይሆናል። ለዛሬ የጥምረቱ ሰብሳቢ የሆነውን አቶ ታደለ ይመር ላጫውታችሁ ፈለኩ። ታዴን የማውቀው ከዛሬ አስራ አምስት አመት በፊት የቀድሞ ዞን ሁለት ( አዲሳአባ በስድስት ዞን የተከፈለች ጊዜ) አስተዳደር ዘርፍ ሀላፊ በነበርኩ ሰአት ነው። ከዛን ጊዜ ጀምሮ የኢህአዴግ አባል ሆኖ ተልእኮ እየወሰደ የሚፈጵም ነው። ተልእኮ የሚሰጡት ደግሞ ” የካዛንችሱ መንግስት” በዞኑ የመደበው ገብረእግዜር ( ” እግዜሩ”) እና ወርቅአበባ የምትባል የስራ ባልደረባችን ነበሩ። ታዴ የአዲሳአባ ፕሬዝዳንት የነበረው አሊ አብዶን ለማሞካሸት ማንም ያልቀደመው ሲሆን፣ አቶ መለስ አሊ ላይ የፓለቲካ ሞት ሲፈርድ ደግሞ ” አሊ አብዶ ዘባተሎ፣ ዝርክርክና ደንታቢስ ” የሚለውን መልእክት ተቀብሎ ለማስተጋባት ታዴን የቀደመው የለም። አሊ እብዱ ተባሮ አርከበ እቁባይ “ምድብ ከንቲባ” ሆኖ ከትግራይ የመጣ ጊዜ ደግሞ ታዴ የአማካሪ ምክርቤት አመራር በመሆን <<ለተወዳጁ ከንቲባ >> ” ከአንፎ እስከ ለገጣፎ” የሚያሰተጋባ ጭብጨባ ያንጨበጭብለት ነበር። በነገራችን ላይ አርከበ በተመደበ በአመቱ ” የውሻ ማሰሪያ የሚያክል ሰንሰለት ወርቅ ለመግዛት” የተቋቋመው ኮሚቴ ሰብሳቢ ታደለ ይመር ነበር። ይህን ሰምቶ የተንጨረጨረው አቶ መለስ የኢህአዴግ አመራር ጠርቶ አርከበን፣ ” ቀለም ቀቢ!፣ በጊዚያዊ ስራ እንጣጥ እንጣጥ የምታበዛ፣ ያለህ አማራጭ ወይ ከጥገኞች ታርቆ መኖር አሊያም መቆረጥ” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጠው። ህዝቡም እንዲያውቅ የስርአቱ አራተኛ መንግስት ለሆነው ሪፓርተር ጋዜጣ እንዲደርሰው አደረገ። ( የሪፓርተርን ዘገባ በአባሪ ይመልከቱ)

የታዴ ጉድ አያበቃም። የመለስ ትሩፋት መጵሀፍ በእጃችሁ ላይ ያላችሁ ሰዎች በገጵ 70 ላይ የታዴን ገድል ታነባላችሁ። በእጃችሁ ለሌለ በከፊል ላቅርብ እና እንሰናበት። በቀጣይ ጊዜ ” የሁለት ምርጫዎች ወግን ያላነበበው ምርጫ ቦርድ” በሚል ርእስ እመለሳለሁ። ለዛሬ የመለስ ትሩፋቶች ታደለ ይመርን በተመለከተ የጳፈችውን እንድትገርቡ እነሆ፣

” እግዜሩ በዞን ውስጥ የሚገኙና ጥብቅ ክትትል የሚደረግባቸውን ተቋማት ማስተር ቁልፍ በማዘጋጀት ዶክመንቶችን ያሰርቃል። ኮፒ ያስደርጋል። ቢሮአቸው እንዲሰበር ካደረጋቸው ውስጥ በወረዳ 21 ጵህፈት ቤት ግቢ ውስጥ የሚገኘው የአዲሳአባ ሴቶች ማህበር፣ የልደታ ቤተክርስቲያንና የኢትዬጲያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ ( ኢሰመጉ) ይገኙበታል። የአዲሳአባ ንግድ ምክርቤትም ከእግዜሩ የስለላ ወጥመድ ማምለጥ አልቻለም። የንግድ ምክርቤቱ የተወያየባቸው አጀንዳዎችና ቃለ ጉባኤዎች በቀጥታ ይደርሱታል። ይህን የሚፈጵምለት ታደለ ይመር የሚባል በንግድ ምክር ቤት ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን ላይ የሚገኝ ሰው ነበር…ልማታዊ ባለሀብት!…

” ታደለ ይመር በንግድ ምክር ቤት ውስጥ የአገልግሎት ዘርፍ ሀላፊ ነበር። ይህ ሳይጠሩት አቤት፣ ሳይልኩት ወዴት የሆነ ሰው በካድሬዎች ዘንድ ” የእርጐ ዝንብ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ነበር። የማይገኝበት ቦታ የለም። በኢትዬጲያ ታሪክ ውስጥ እጅግ አሳፋሪ ተግባሮች ከፈፀሙ ሰዎች አንዱ ነው። በተለይም በኤርትራ መገንጠል ወቅት የኢትዬጲያን ህዝብ ወከለ ተብሎ ኤርትራ በመሄድ << እኛ የኢትዬጲያ በተለይም የአማራ ተወላጅ የሆንን ሰዎች ስለፈፀምንባችሁ ግፍና በደል ይቅርታ እንጠይቃለን>> የሚል ንግግር አድርጓል። ቅሌት አንዴ ከጀመረ አይለቅምና የኢትዬ -ኤርትራ ጦርነት ሲጀመር ደግሞ ንግድ ምክር ቤቱን በመወከል << ሻእቢያ ይደመሰሳል!!፣ የኤርትራ ህዝብም ልኩን ያውቃል!>> የሚል ቀራርቶ አሰምቷል።…
ታደለስ ታድሏል…
የማይጣላ ጭንቅላት
ተሸክሞ ይዞራል።”

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.