ከሻቢያ ሥርዓት ለኢትዮጵያ ሥርዬት ይመጣል ብሎ ማመን አንድም ቂልነት፣ አልያም መሠሪነት ነው! – በአሞራው ውብነህ

በአሞራው ውብነህ (amorawwubneh1933@gmail.com)፣

isayas-on-esatሰሞኑን በሁለት የተለያዩ ጸሐፊዎች ሁለት እጅግ ተቃራኒ የሆኑ መጣጥፎች ለንባብ በቅተዋል። የጽሑፎቹ ጭብጥ የሚያቀነቅነው“ሻቢያ ለኢትዮጵያውያን የነፃነት ትግል እውነተኛ አጋር ሊሆን ይችላል? ወይስ ምንጊዜም ሊታመን የማይችል መሠረታዊ ጠላት ነው?» በሚሉ ኃሣቦች ዙሪያ ነው።

ከሻቢያ መሠረታዊ ባህርይ በመመርኮዝ፣ በአሉታዊው ሁኔታ ትንታኔ ያቀረቡት አቶ አንዱዓለም ተፈራ ናቸው። የ”እስከመቼ» ድረገፅ ባለቤት እና አዘጋጅ የሆኑት አቶ አንዱዓለም “ለፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቅ ምስክር»[i] በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፋቸው፣ እርሣቸው አባል የነበሩበት የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሠራዊት (ኢሕአሠ) ተዋጊ ሆነው በትግራይ፣ በኤርትራ እና በጎንደር ክፍለሀገሮች ከዚያም ድንበር ተሻግረው በሱዳን አገር በሚዘዋወሩበት ወቅት ያጋጠማቸውን፣ ያዩትን እና የተገነዘቡትን አንድ በአንድ እየተነተኑ፣ ማስረጃ በማጣቀስ አቅርበዋል። እንደእርስሣቸው ምሥክርነት ሁኔታውን፦

“ከሁሉ በላይ የተማርኩት፤ ኢሳያስ አፈወርቂ ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ ነው። በርግጥ ቀደም ብሎ በኢሕአፓ ላይ የፈጸመው በደል በውል የተመዘገበ ነው። ባጠቃላይ ግን ለኢትዮጵያ ያለው ጠንካራ ጥላቻ፤ ጊዜ የማይሽረው፣ ምንም ዓይነት ድርድር የማያረግበው፣ እና በደም ሥሩ የተተከለ ስለሆነ፤ ከዚህ ግለሰብ ጋር የሚደረግ ቃለ መጠየቅም ሆነ ከሱ የሚደመጥ በጎ ንግግር ዋጋ የለውም። በርግጥ ከአንድ ድርጅት የግል ፍላጎት ተነስቶ፤ ኢሳያስን እንደጣዖት ማጋነን ይቻላል። ተሸክሞ ማተለቅም ይቻላል። ምሽግ ሠጠኝ፣ ማሰልጠኛ ቦታ አቀረበልኝ፣ ገንዘብ ረዳኝ ብሎ ከሱ መጠጋት፤ የወደፊትን የሀገር አደጋ አለማጤን ስለሆነ፤ እንዲህ ባለ ተግባር ላይ የተሰማሩትን ተው! ተብለው እንዲሰሙ ማድረግ ተገቢ ነው። እምቢ ካሉ ግን፤ ሀገራችንን ሊሸጡ ተነስተዋል ብሎ መኮነን ያስፈልጋል። ከጠላት ጋር አብረዋል ብሎ መወንጀል ያስፈልጋል።»

በማለት ይገልጹታል። አቶ አንዱዓለም ተፈራ ስለሻቢያ እና መሪው ኢሣያስ አፈወርቂ በተጨባጭ የተገነዘቡትን እውነታ በዐይን እማኝነት ተመስርተው ምሥክርነታቸውን ሲያቀርቡ፣ በተቃራኒው ወገን የቆሙ ሌላ ሰው ደግሞ ይህንን አቋም በማጣጣል ብቅ ብለዋል። እኒህ ሰው አቶ ኃይለአብርኤል አያሌው ይባላሉ።

አቶ ኃይለአብርኤል ከሁሉ ያስቀደሙት ከዚህ በፊት በፖለቲካ እና የሲቪክ ድርጅቶች ውስጥ የነበሯቸውን ሥልጣኖች በማስተዋወቅ ነው፦ የቀድሞው የመዐህድ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ፣ የሕብረት ም/ሊቅመንበርና የሞረሽ መስራች አባል[ii]» በማለት ራሣቸውን በማስተዋወቅ ይጀምራሉ። በእርሣቸው አገላለጽ መሠረት “የዐማራውን ስም የማጉደፍ እና የማጠልሸት ፕሮፓጋንዳ የተጀመረው በኤርትራ በረሃዎች ነው።» ለዚህ ደግሞ “የኤርትራ ተገንጣይ ድርጅቶች [ሻቢያን ጨምሮ ማለት ነው] የትግራይን ነፃ አውጪ ግንባር በማስታጠቅ በኢትዮጵያ ላይ የውክልና ጦርነት እንዲከፍት» ማድረጋቸውን በራሣቸው አንደበት አምነዋል። አሁን እርሣቸው ከጊዜ በኋላ ስለ ኢሣያስ አፈወርቂ እና ስለሚመራው ሻቢያ “ለኢትዮጵያ ቅን አሣቢነት» የተገለጸላቸው ሚሥጢር ግን የዚህ የቀድሞ አቋማቸው ጋር ሲነፃፀር ፍፁም ተቃራኒ የሆነ ነው። በአሁኑ የፖለቲካ አቋማቸው መሠረት፦

“ሻብያ ወይም አሁን አለምዓቀፍ እውቅና ያለው የኤርትራ መንግስት ለረጅም ዘመን ባካሄደው ትግል ውስጥ አንግቦት የነበረው አብዛኞቹ መፈክሮች በግዜ ሂደት ወይበው በሁኔታዎች ተጽዕኖ ተለውጠው በተፈጠረው አዲስ የሃይል አሰላለፍ ውስጥ ዋና የህልውናው ጠላት ሆኖ በተገኘው በትላንት ተላላኪው ሕወሓት ወያኔ ጋር የጌታና ሎሌነቱ ዘመን እብቅቶ በጦርነት ፍጥጫ ውስጥ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት በተፈጠረው የሃይል መሳሳብና ባለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ተንተርሰው አዲስ የወዳጅነት ምዕራፍ የከፈቱት ኢትዮዽታዊ ሃይሎች አማራጭ የትግል ስልታችውን ገቢራዊ ለማድረግ ከኤርትራው መንግስት ጋር እያደረጉ ያለው ግንኙነት በኢትዮጽያውያን ዘንድ በድጋፍና ተቃርኖ መሃከል ሲዋዥቅ ቆይቶ በአሁኑ ወቅት በኢትዮዽያ ውስጥ ባለው ዘረኝነት የፖለቲካ እመቃና የነጻነት እጦት የሰላማዊ ትግሉን ምህዳር እጅግ ያጠበበው ከመሆንም በላይ በሰላማዊ መንገድ ለውጥ ይገኛል የሚለው ተስፋ ጭለማ የዋጠው በመሆኑ አብዛኛው ኢትዮዽያዊ በኤርትራ የተጀመረውን እንቅስቃሴ የመደገፍ አዝማሚያ እያሳየ ያለበት ወቅት ላይ ነን።»

በማለት አንባቢዎቻቸውን ለማማለል ጥረዋል። ጥረቱ ባልከፋ፤ ሆኖም ነገሩ “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ» ሆነ። ለመሆኑ እንዲህ ለሻቢያ ጥብቅና የቆሙት አቶ ኃይለገብርኤል አያሌው ማን ናቸው?

እኒህ ሰው አሁን የት እንደሚኖሩ በግልጽ ባያሣውቁም ከዚህ ቀደም ብሎ በኢሣት ካደረጉት ቃለመጠይቅ በመነሣት ዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ መሽገው እንደሚኖሩ የአደባባይ ምሥጢር ነው። ሆኖም ከቀድሞ ድርጅቶቻቸው ኃላፊነቶቻቸው እንዴት እንደተለያዩ ግልፅ አላደረጉም። በዚህ ረገድ አቶ አንዱዓለም ስለራሣቸው ሲገልጹ ምንም ሳያፍሩ ከድርጅታቸው ከኢሕአፓ መቼ እንደተለያዩ ይፋ አድርገዋል። ስለሆነም ለአቶ ኃይለአብርኤል በመጀመሪያ ደረጃ ሊቀርብላቸው የሚገባው ጥያቄ “ከእነዚህ ከጠቀሷቸው (ምናልባትም ካልጠቀሷቸው) የቀድሞ የኃላፊነት ቦታዎችዎ እንዴት እና በምን ምክንያት ለቀቁ?» የሚል ነው። መቼም በአሁኑ ዘመን እንደሆቴል አልጋ ተከራይ ከአንዱ ድርጅት ወደሌላው፣ አንዳንዴም በአንድ ጊዜ የብዙ የፖለቲካ እና የሲቪክ ድርጅቶች አባል መሆን የብልጥነት መለኪያ ተደርጎ ተወስዶ ይሆናል። ነገር ግን እዚህም፣ እዚያም መርገጥ የፖለቲካ ዓላማ ጽናትን አመልካች ሊሆን አይችልም። ስለሆነም እርሣቸው አሁን በሚያምኑበት ሻቢያን ” የኢትዮጵያ ነፃነት እና አንድነት ብቸኛ ጠበቃ እና አቀዳጅ» መሆኑን በሚያሣየው የትግል መሥመር ታግለው እስከዛሬ ምን ውጤት እንዳስገኙ ለአንባቢዎቻቸው በተጨባጭ ሊያቀርቡ ይገባል። አልያ ግን ሁሉንም ሻቢያን የሚቃወሙ ኢትዮጵያውያንን፣ በተለይም ዐማራውን ከፈፅሞ ጥፋት ለመታደግ የተቋቋመውን ሞረሽ ወገኔን እና የድርጅቱን መሪ አቶ ተክሌ የሻውን፦

” እንደ አለመታድል ትልቁን ሕዝባዊ ተልዕኮ ለማሳካት የግል ስሜትን ተቆጣጥሮ ያነገቡትን እላማ ከማስቀድም ይልቅ ትንንሽ የንትርክ ሰበዞችን መምዘዝ በሚያስቀድሙ፤ አዲሱን ትውልድ ለማድመጥ ጆሮዋችው የተደፈነና እንቆምለታለን የሚሉትን ወገን የማይወክል ፤ጥበብ የራቀውና ዲፕሎማሲያዊ አቀራረብ የተለየው ፖለቲካ በማራመድ ተለዋዋጩን የአካባቢያችንን ሁኔታ ገምግሞ ተመጣጣኝ አቋም ይዞ መገኘት በሚያስፈልግበት ወቅት በአሮጌ የታሪክ ቡሉኮ ተጀቡኖ ዘመኑን ያልዋጀ ሃሳብ ይዞ አማራን ያህል ህዝብ አደራጃሁ ብሎ ማሰብ ቀልድ መሆኑ ሊገባችው አለመቻሉ ያስዝናልም፤ ያሳፍራልም።»

ብሎ ማንጓጠጥ የፖለቲካ ብስለትን አያመለክትም።

ለዐማራው ተወላጅ፣ የሻቢያው መሪ አቶ ኢሣያስ አፈወርቂም ሆነ ሟቹ የወያኔዎቹ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው። ለእኒህ አምባገነኖች “የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ የተጻፈው ሁሉ የዐማራ ደብተሮች የለቀለቁት ተረት ተረት ነው፤ ኢትዮጵያም ከመቶ ዓመት ያልበለጠ ታሪክ ያላት ምኒልክ የፈጠራት ናት።» የእነርሱ ደቀመዝሙር መሆናቸውን በአደባባይ ያወጁት አቶ ኃይለገብርኤል አያሌውም የዐማራው ድርጅት የሞረሽ ወገኔ መሪዎች “በአሮጌ የታሪክ ቡሉኮ የተጀቦነ» ናቸው። አቶ ኃይለገብርኤል ባላዩት እና በማያውቁት ነገር ስለሻቢያ ቅዱስነት እና ለኢትዮጵያውያን የነፃነት ትግል አጋርነት ይህን ያህል ገፍተው ጥብቅና ቆመዋል። ሆኖም ሻቢያን ጠንቅቀው የሚያውቁት እና “በሻቢያ ድጋፍ ወያኔን ታግለን መጣል እንችላለን» ብለው አምነው ወደ ኤርትራ አቅንተው የነበሩት ግለሰቦች የሚሰጡት የዐይን ምስክርነት የእርሣቸውን ተቃራኒ ነው።

በተለያዩ ጊዜያት “የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር» በመባል በሚታወቀው ድርጅት በአመራር ላይ የነበሩ እና ያሉ፦ ፕሮፌሠር ሙሤ ተገኝ፣ አቶ መልኬ መንግሥቴ፣ አቶ ልዑል ቀስቅስ (በ1997 ዓ.ም ምርጫ የፓርላማ ተመራጭ ነበሩ)፣ አቶ አሰፋ ኃይሉ (በዐማራ ክልል የምክር ቤት ተመራጭ የነበሩ)፣ እና ሌሎችም በተደጋጋሚ እንደገለጹት ሻቢያ ምንጊዜም ጠላትነቱ የማይሽር ፀረ-ኢትዮጵያ እና ፀረ-ዐማራ ድርጅት ነው። እኒህ ሰዎች በሻቢያ ዕርዳታ ወያኔን እናስወግዳለን ብለው፣ ከሁለት እስከ አሥር ዓመታት በኤርትራ በረሃዎች ተንከራትተው ነበር። ሆኖም አቶ ኃይለገብርኤል ጥብቅና የቆሙለት ኢሣያስ አፈወርቂ እና ጭፍሮቹ አንዲት ጋት እንኳ አላንቀሣቅሳቸው ስላሉ ተስፋ ቆርጠው እና ሕይዎታቸውን አስፈላጊ ባልሆነ ሁኔታ እንዳያጡ በመስጋት ዳግም ተሰድደዋል።

በቅርብ ጊዜ ከግንቦት 7 ወታደራዊ ክንፍ ተለይተው ከወጡት አባሎች መካከል፦ ሽታዬ (የቅፅል ስም ቼጎቬራ፣ የወታደራዊ ክንፉ የአስተዳደርና ፋይናንስ ኃላፊ የነበረ)፣ ማስረሻ (የቅፅል ስም አባስ፣ የወታደራዊ ሥልጠና ኃላፊ የነበረ)፣ ኮስሞስ (የወታደራዊ ክንፉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረ)፣ ቴዎድሮስ ስዩም ኃይሌ (የቅፅል ስም ምኒልክ)፣ እና ሌሎችም ወደ ኤርትራ አቅንተው የግንቦት 7 ታጣቂ ኃይልን ከተቀላቀሉ በኋላ የሻቢያን የእገታ ሕይዎት አምልጠው ወጥተዋል። ስለሻቢያ መሠሪነት እና ፀረ-ኢትዮጵያነት እኒህ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የሰጡትን የዐይን እማኝነት አቶ ኃይለአብርኤል እስከዛሬ አልሰሙ ይሆን?

ምክር ለአቶ ኃይለአብርኤል፦ የዐማራውን ወጣት ለሻቢያ እና ለወያኔ የሥውር ሤራ የዕርድ ጉረኖ ከሚያቀርቡ እርስዎ ራስዎ ወደኤርትራ ሄደው ትግል ይጀምሩ እና ምሣሌ ይሁኑ። ምናልባት ከተሣካልዎት ተከታዮች ያገኙ ይሆናል። ሆኖም እርስዎ ከጀርባ ሆነው ብሶት ላይ ያለውን ዐማራ ለሌላ የከፋ ዕልቂት አይግፉት።

በዚህ የታሪክ አጋጣሚ ተጠቅመው፣ በኢትዮጵያውያን በጠቅላላ እና በተለይም ደግሞ በዐማራው ተወላጆች ላይ በተጋረጠው የኅልውና አደጋ ላይ የሚሣለቁትን ዝም ብሎ ለማለፍ አይቻልም። ስለዚህ “በሻቢያ ድጋፍ በወያኔ ላይ የትጥቅ ትግል አካሂደን ኢትዮጵያን ነፃ እናወጣለን» የሚሉ “የአየር በአየር ፖለቲከኞች» አደብ ሊገዙ ይገባል።

በተለይ ለዐማራ ወጣቶች፦ ዐማራው በታሪኩ ካጋጠሙት የኅልውና ፈተናዎች መካከል ባለፉት 24 ዓመታት ያለፈበት እጅግ የተወሳሰበው ምዕራፍ ነው። ስለሆነም ይህንን የፈተና ጊዜ ለማለፍ ጽናትን እና በራስ መተማመንን ይጠይቃል። በተለይ ደግሞ ለዐማራው እና በጠቅላላ ለኢትዮጵያውያን መሠረታዊ እና ታሪካዊ ጠላቶች ከሆኑት እንደ ሻቢያ ዓይነት ድርጅቶች ሥርዬት ይገኛል ብሎ ማመን፣ አንድም ቂልነት ሲከፋም እጅግ መሠሪነት ነው። በመሆኑም የዐማራ ወጣቶች ከእንዲህ ዓይነት ዓላማ አራማጅ፣ ኃሣይ መሢኃን ከሆኑ የሣር ውስጥ እባቦች ራሳቸውን ሊያርቁ ይገባል።

በአሞራው ውብነህ (amorawwubneh1933@gmail.com)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.