ኢትዮጵያዊነት መፍትሄ ነው-ከአብርሃም  ዘ.ታዬ

መነሻው ከአርባ አመት  በፊት ህወሃት/ ወያኔ   የተቋቋመው  የተነሳበትን ክልል “የትግራይ ነጻ አውጪ” በሚል  ነው። ስታሊናዊ  ርዕዮተ አለምን  አንግቦ የተነሳ ስለሆነ በዘረኝነት አርንቋ ተበክሎ በፋሺስታዊ ማን አለብኝነት ነውልሎ ከትግራይ ደረቅ መሬት የበለጠ ሌላውን የ ኢትዮጵያ መሬት ጨምሮ ማስተዳደር ፈለገ። ከዛም ቋንቋን ብቻ ዘውግ መሰረት ባደረገ የከፋፍለህ ግዛ ስልቱ በሚመቸው መንገድ መድቦናል። ከሃያ ሶስት አመት በላይ  እኛ አላስተዋልንም እንጂ ለምሳሌ የሃረሪ ክልል መንግስት ማለት እንደ አንድ የአፍሪካ ሃገር መንግስት ማለት ነው። እንደዚሁም  ክልሉን ሲከፋፈሉ አብሮት ለነበረው ኦነግ  ኦሮሚያን መገንጠል እምቢ አላቸው እንጂ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ማለት እንደ 54ተኛ የአፍሪካ ሃገር እንዲቆጠር የተጠነሰሰ  ሃገርን እንደ ዝክር ድፎ ዳቦ የመበጣጠስ ሴራ ነበር። ይህንንም ሴራውን ያስፈጽሙለት ዘንድ ጠባብነትን በመዋጋት የሚታወቁትን ለመስለብ አሁን ደግሞ የቤተ አምሃራ ክልል እያለ ካርታ እየሰራ ሊከልለን ቆርጦ ተነስቷል።የተሸረበልንን ዝም ብለን ካየነው ጎረቤታችን ሶማሊያ በአንጃዎች ተከፋፍላ ጥላቸው የሰፈር ጥል እንደሆነው ሁሉ ወይም በአውሮፓ በጎሰኝነት የተነሳ ተበታትና እንደቀረችው አልባንያ ኢትዮጵያ የሚለው ቀርቶ በጣም ወርዶ በጎጥ ሊያጫርሰን ተሰናድቷል።

የክልላዊነት መዘዙ በጣም ከመዝቀጡ የተነሳ የኦሮሞ ከብት አርቢ ለከብቶቹ ግጦሽ ፍለጋ ወደ ሱማሌ ድንበር ከተሻገረ እንደ ባዕድ ተቆጥሮ ተኩስ ይከፈትበታል፤ አፋር ወደ ኢሳ ከተሻገረ ይገደላል፤ ለቤነሻንጉል በተከለለ ክልል የሰፈረ የአማራ አርሶ አደር የደከመበትን አንጡራ ሃብት ተቀምቶ ይባረራል፤ አኝዋክ ለዘመናት ተከባብሮና ተቻችሎ ከኖረው ከኑዌር ወንድሙ ጋር እንዲጋጭ ተደርጎ በገላጋይነት ሥም የፈደራል ፖሊስና የጸጥታ ሃይል በጅምላ እንዲጨፈጭፈው ይፈረድበታል። በመልካም አስተዳደር እጦት የደረሰበትን መከራና ስቃይ አብሮ ሲጋፈጥ የኖረው የወልቃይት ጠገደ ህዝብ አንተ አማራ አንተ ትግሬ በሚል የዘር ክፍፍል ለመገዳደል ካራውን ስሎ ተቀምጦአል።  ይህ አልበቃ ብሎም የአንድ ብሄር አባላትን በጎሳ ሸንሽኖ የጉጂ ኦሮሞ ከአርሲ ወንድሙ ጋር ደም እንዲቃባ ተደርጎአል።

ሰብኣዊነት ካልጎደለን በስተቀረ አብዛኛው የኢትዮጵያ ተወላጆች እስቲ ራሳችሁን ከዛም ጎረቤታችሁን አስቡ። ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ቋንቋ ወይም ዘውጌ ማህበረሰብ ያለባት ሃገር ስለሆነች ለሁሉም በዘር የተመሰረተ ክልል መፍጠር ከባድ እንደሆነ ትረዳላችሁ።ሃገርን ማፍረስ ዕቅዱ አድርጎ ለተነሳው ለወያኔ ይህ ከባድ ጉዳይ ጉዳዩ አይደለም።

 

ወያኔ በጉልበት የጫነብን የመከፋፈልና የመለያየት አደጋ አንድ ቀን ሲያበቃ የነጻነት ብርሃን ፈንጥቆ በሠላምና በመቻቻል የምንኖርበት አገር እንኳ እንዳይኖረን በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች መጠነ ሰፊ የሆነ ድንግል መሬታችንን ለህንድ፤ ለቻይናና ለአረብ ከበርቴዎች በርካሽ ዋጋ በመቸብቸብ በገዛ አገራችን የባዕዳን አሽከሮች ሆነን እስከ ዘለአለሙ እንድንኖር መሠረት ተጥሎአል። በደልና መከራው እንዲያበቃ በአገዛዙ ላይ የተቃውሞ ድምጹን ያሰማ ከሥራውና ከኑሮው ተፈናቅሎ በድህነት አረንቋ ውስጥ እንዲጣል አለያም እየታደነና የሽብርተኝነት ታፔላ እየተለጠፈበት ወደ የማጎሪያ ጥቢያዎች እንዲወረወር ተደርጎአል።ዘረኝነቱ ሌሎቹን ነዋሪዎቹን በማስወገድ ላይ የመሰረተ ብቻ ሳይሆን እትብታቸው የተቀበረበትን ለምለም አፈር ሳይቀር እያጫኑ የሚያለሙት የራሳቸውን ክልል ብቻ ነው።በመከላካያው ዘርፍ ሆነ በሲቪል መስሪያ ቤቶች ሳይቀር የበላይ ሹመቶች የተያዙት በህወሃት ወያኔ ሰዎች ብቻ ነው።ልማቱ በሁሉም ክልል እኩል መሆን ሲገባው የነሱ ሲለማ የሌላው ይደማል።

 

በዘርና በቋንቋ ከተከለለልን ክልል  ኣልፈን ለመኖር፤ ስራ ለመቀጠር ዘር ይመረጣል።  ሲከፋም በትዳር አማት የሚሆናቸውን ሰው ቅድሚያ “ብሄሩ ወይም ብሄሯ” ምንድን ነው ብለው የሚጠይቁ ሳያውቁም ይሁን ኣውቀው የሰርጉ ታዳሚዎችም ሳይቀሩ ድግሱን እየኮመኮሙ የጥንዶችን “ብሄር” የሚያሙ የወያኔ ጠባብነት ዘረኝነትን የሚያስፈጽሙ ትውልዶች አሉ።

ለመሆኑ ብሄርህ ወይም ብሄርሽ  ምንድን ነው ተብላቹ ስትጠየቁ ብሄሬ ኢትዮጵያ ነው ብላቹ ብትመልሱ በጣም ትክክል እንደሆናቹ ታውቃላችሁ ? ምክንያቱም ብሄር የሚለው ቃል ከግዕዝ ቋንቋ የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙ ሃገር ማለት ነው።  በእውነትም ብሄራችን ሃገራችን  ኢትዮጵያ ናት።ብሄረሰብዕ ማለትም የሰው ሃገር ማለት ነው።እውነታው ይህ ሆኖ እያለ ዘመነኛው ገዢ ትርጉሙን ስቶት እኛንም ለሃገር ሳይሆን  በዘር መነጽር ብቻ እንድናይ አድርጎናል።

ከሁሉም በላይ ትኩረት መሰጠት ያለበት ግን የዜግነታችን ክብር ከጎሳ ማንነት የሚበልጥ መሆኑን ማወቅ ነው። ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ከተገዢነት አልፎ በዜግነት ደረጃ የታዩበት አንድም ጊዜ የለም።ይባስ ተብሎ ዘመን አመጣሹ ህወሃት በየቀበሌው መታወቂያችን ላይ ከዜግነት ወርዶ ዘረኛነትን ይጽፋል።መታወቂያዉም ቢሆን ያለፉት መንግስታትት ከሚወረውሩልን የዜግነት መብት ፍርፋሪ አንዱ ብቻ ነበረች። ከዛቸው ፍርፋሪ ላይ የብሄርተኝነት መርዝ ጨምሮበት  በሩዋንዳ ሁቱ ነህ ቱትሲ ነህ ተባብለው እንደተፋጁት ወያኔ ህወሃት እኛንም ለማፋጀት ተሰናድቷል ብቻ ሳይሆን ከጋምቤላ የተጨፈጨፉት ኑዌሮች በሃረር በበደኖ አማራ ተብለው በጅምላ በቅርቡ ያለቁት የዚህ ዘረኝነት ዉጤት ነው።

ለመሆኑ ኢትዮጵያዊነት ማለት ትርጉሙ መፍትሄ እንደሆነ ያውቃሉን? አፍሪካውያን በባርነት ተይዘው እያለ ነጻነት ያመጣላቸው የነማርኮስ ጋርቬይ ኢትዮጵያኒዝም ጽንሰ ሃሳብ ነው። ኢትዮጵያዊነት ፓን አፍሪካኒዝም አንድነት ነው። አለም በግሎባላይዜሽን አንድ እየሆነች ይልቁንም የአፍሪካ አንድነት መስራችና መቀመጫ ሃገርን የመገነጣጠል አብነት ልትሆን  አትችልም። በ ሌላው አለም የማይጣጣሙት የእስልምናና ክርስትና ተከታዮች ዘመዳሞች ሆነው በፍቅር የሚኖሩበት፤የመቻቻል፤ደሃም ቢሆኑ ተካፍሎ የመኖር ትልቅ ፈሪሃ እግዚአብ ሄር ባህል የበለጸገባት ኢትዮጵያ ናት።ወያኔ እንኳን ሊያጠፋው ያልቻለውን የስንት ሺ ዘመናት አብሮነት ማስጠበቅ እየቻለን ለምን የነሱ መሳሪያ እንሆናለን?

ጎጠኛነት ከኢትዮጵያዊነት ጋር አይወዳደርም ለክልላዊነት መፍትሄው ኢትዮጵያዊነትን ማስተጋባት ነው።

 

ከ አብርሃም   ዘ. ታዬ blogger at www.zethiopians.blogspot.com

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.