ገንዘቤ ዲባባ በሞናኮ የእድሜ እኩያዋ ሊሆን የተቃረበውን የ1500ሜ. ሪኮርድ ሰበረች – ብዙአየሁ ዋጋው

አንድ የዓለም ሪኮርድ እና ስድስት የውድድር ስፍራው ሪኮርዶች የተሻሻሉበት እንዲሁም ሰባት የወቅቱ ፈጣን ሰዓቶች የተመዘገቡበት የ2015 ሞናኮ ዳይመንድ ሊግ የዕለቱን ልዩ አቋም ያሳየችው ገንዘቤ ዲባባ በሴቶች 1500ሜ. 3፡50.07 የሆነ አዲስ የዓለም ሪኮርድ በማስመዝገብ ያሸነፋችበት እና ስሟ በዓለም ዙሪያ በስፋት ሲያስተጋባ ያመሸበት ሆኗል፡፡

በቻይናዊቷ ኩ ዩኒያ በ1993 ተመዝግቦ ላለፉት 22 ዓመታት ያህል ሳይደፈር የቆየውን 3፡50.46 የሆነ ሰዓት በ39 ማይክሮ ሰከንዶች ያሻሻለችው  ገንዘቤ  በሞናኮ ሪኮርዱን ለመስበር የነበራትን ዕቅድ እንድታሳካ አሯሯጯ የነበረችው የዓለም የቤት ውስጥ 800ሜ. ሻምፒዮኗ ቻኔሌ ፕሪስ የሚጠበቅባትን ሁሉ በአግባቡ ተወጥታለች፡፡ ቻኔሌ ፕሪስ ገንዘቤ የመጀመሪያውን ዙር በ60.31 ሰከንድ እንዲሁም 800 ሜትሩን በ2 ደቂቃ ከ04.52 ሰከንድ እንድትሮጥ ካገዘቻት በኋላ የወጣች ሲሆን የአውሮፓ ሻምፒዮኗ ሲፋን ሀሰንን ከበስተጀርባዋ አስከትላ ግቧ ካደረገችው ሰዓት ጋር መፎካከሯን የቀጠለችው ገንዘቤ መቶ ሜትር ያህል ሲቀራት ቢያንስ ቢያንስ የዓለም ሪኮርዱን የሚስተካከል ሰዓት ማስመዝገብ እንደምትችል ግልፅ ሆኖ ነበር፡፡

የሁለት ግዜ የዓለም የቤት ውስጥ የ1500ሜ. እና 3000ሜ. ሻምፒዮኗ ገንዘቤ ከታላቅ እህቷ ጥሩነሽ ዲባባ ለየት የሚያደርጋትን ሌላ ትልቅ ዓለማቀፋዊ ስኬት የማስመዝገብ ሕልሟን ከግቡ ለማድረስ ጥርሷን ነክሳ ሮጣ በአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ የዓለም ሪኮርዶች መዝገብ ላይ ከሰፈሩት ሰዓቶች ለመስበር  በጣም  የሚከብደውን ሪኮርድ ልታሻሽለው በቅታለች፡፡ የገንዘቤ የ1500ሜ. ሪኮርድ በቤት ውጭ የመካከለኛ ርቀት በኢትዮጵያዊት አትሌት የተመዘገበ የመጀመሪያ ሪኮርድም ሆኗል፡፡
ከአስደሳች ድሏ በኋላ ከሞናኮ በስልክ አስተያየቷን የሰጠችን ገንዘቤ ‹‹በውድድሩ ላይ ከእኔ ዕድሜ ጋር ተቀራራቢ የሆነ ግዜ ያስቆጠረውን ሪኮርድ የመስበር ዕቅዱ የነበረኝ ቢሆንም ወደውድድሩ ከመግባቴ በፊት አስብ የነበረው ግን ከ3 ደቂቃ ከ54 ሰከንድ በታች መሮጥን ነበር፡፡ ሆኖም በመጨረሻ ሪኮርዱን  ልሰብረው  በቅቻለሁ፡፡  ወደውድድሩ የገባሁት ስለሌሎቹ ተፎካከሪዎች ምንም ሳላስብ በራሴ ሩጫ ላይ ብቻ ለማተኮር ወስኜ ነው፡፡ ናይኪ በደንብ ልታግዘኝ የምትችል አሯሯጭ ስላዘጋጀልኝ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ዙሮች በጥሩ ሁኔታ የሮጥኩ ሲሆን እርሷ ከወጣች በኋላ ሌሎቹ አትሌቶች ሊቀድሙኝ እንደማይችሉም የእርግጠኝነት ስሜቱ ነበረኝ›› ብላለች፡፡
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተሳተፉባቸው ሌሎች ውድድሮች ላይ የተመዘገቡትን ውጤቶች ስንመለከት በወንዶች 800ሜ. ምንም ግምት ያልተሰጠው ቦስኒያዊው አመል ቱካ በ1፡42.51 ቦትስዋናዊውን ኒጄል አሞስ እና ጅቡቲያዊው አያንለህ ሱሌይማን አስከትሎ በቀዳሚነት አጠናቋል፡፡ መሀመድ አማን በ1፡44.09 ስምንተኛ ወጥቷል፡፡ በወንዶች 1500 ሜ. ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበረው አማን ወቴ የዓመቱ የግል ምርጡ በሆነ 3፡30.29 ስምንተኛ ሀኖ ጨርሷል፡፡ በሴቶች 1500ሜ. ፉክክሩ ገንዘቤን ተከትላ ሁለተኛ በመሆን ያጠናቀቀችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድ ተወካይ ሲፋን ሀሰን የጨረሰችበት 3፡56.05 እና ሶስተኛ የወጣችው አሜሪካዊቷ ሻኖን ሮውበሪ የገባችበት 3፡56.29 የየሀገሮቻቸው ብሔራዊ ሪኮርድ ሆነዋል፡፡ በርቀቱ ከገንዘቤ በተጨማሪ ተሳታፊ የነበሩት ኢትዮጵያውያኑ በሱ ሳዶ እና አአክሱማይት እምባዬ በስም ቅደም ተከተላቸው መሰረት ሰባተኛ እና አስራ ሶስተኛ ወጥተዋል፡፡
ኬንያዊው ካሌብ ንዲኩ በ7፡35.13 በበላይነት ባጠናቀቀበት የወንዶች 3000ሜ. የኔው አላምረው የዓመቱ የግል ምርጡ በሆነ 7፡36.39 ሁለተኛ ወጥቷል፡፡ ያሲን ሀጂ 9ኛ እንዲሁም ደጀኔ ጎንፋ 11ኛ ሆነው ጨርሰዋል፡፡ በሴቶች 3000ሜ. መሰናክል ውድድር ላይ ተካፋይ ከነበሩት ሕይወት አያሌው 4ኛ፣ ብርቱካን ፈንቴ 11ኛ ሆነው ጨርሰዋል፡፡
በሌሎች ትኩረት ያገኙ ውድድሮች የዳይመንድ ሊጉ የነጥብ ፉክክር አካል ባልነበረው የወንዶች 1500ሜ. ኬንያዊው አስቤል ኪፕሮፕ የዓለም ሪኮርዱን ለመስበር አንድ ሰከንድ በቀረው 3፡26.69 ቀዳሚ ሆኖ ሲጨርስ አልጄሪያዊው ቶፊቅ ማክሉፊ በ3፡28.75 ሁለተኛ ሞሮኳዊው አብደላቲ ኢጉዲር በ3፡28.79 ሶስተኛ ወጥተዋል፡፡ ኪፕሮፕ የገባበት ሰዓት የውድድር ስፍራውን ሪኮርድ ያሻሻለ ሲሆን ተከታዮቹን ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁት አትሌቶች የጨረሱበት ሰዓትም የራሳቸው ምርጥ ሆኖ ተመዝግቦላቸዋል፡፡ እንግሊዛዊው ሞ ፋራህ በዚህ ፉክክር ላይ በ3፡28.93 አራተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡ በወንዶች 100ሜ. አሜሪካዊው ጀስቲን ጋትሊን ያሸነፈበት 9፡78 እንዲሁም በሴቶች 3000ሜ. መሰናክል ቱኒዚያዊቷ ሀቢባ ጋሪብ ያሸነፈችበት 9፡11.28 በውድድር ስፍራው ሪኮርድነት ከተመዘገቡት የትራክ ላይ ውጤቶች ይጠቀሳሉ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.