የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለብይን ተቀጠሩ

‹‹የታሰርኩት ቤተሰቦቼን በእሳት አቃጠሉብኝ ብዬ ስለከሰስኩ ነው›› አቶ አንጋው ተገኝ

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት የተከሰሱት 16 የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለሀምሌ 17/2007 ዓ.ም ለብይን ተቀጠሩ፡፡ አመራሮቹ ሀምሌ 1/2007 ዓ.ም በጠበቆቻቸው በኩል የክስ መቃወሚያና የዋስትና ጥያቄ አቅርበው የነበር በመሆኑ ዛሬ ሀምሌ 13/2007 ዓ.ም አቃቤ ህግ ለጥያቄው መቃወሚያ እንዲያሰማ ቀጠሮ ተሰጥቶት የነበር ቢሆንም ሳይቀርብ ቀርቷል፡፡

በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ ጠበቃዎች ባቀረቡት ጥያቄ ላይ አቃቤ ህግ ተቃውሞ ባለማቅረቡ ደንበኞቻቸውን በሽብር ወንጀል ያልተሳተፉ በመሆናቸው በሽብር ወንጀል መከሰሳቸው ትክክል አለመሆኑን፣ ቢቻል ክሱ ተዘግቶ እንዲሰናበቱ፣ ይህ ባይሆን እንኳ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው በውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ያቀረቡትን ጥያቄ መሰረት አድርጎ ብይን እንዲሰጥላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም አቃቤ ህግ በችሎቱ አለመገኘቱና ለጥያቄው መልስ አለመስጠቱ ጥያቄዎቹን መቃወም አለመፈለጉን ስለሚያሳይ ለሀምሌ 17/2007 ዓ.ም የተከሳሾቹ ጠበቆች ባቀረቡት ጥያቄ ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾቹ የሰማያዊ፣ የቀድሞው አንድነትና የመኢአድ አመራሮች ናቸው፡፡

ተከሳሾቹ እስር ቤት ውስጥ በደል እየተፈፀመባቸው እንደሆነ አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን የቀድሞው አንድነት የሰሜን ጎንደር አመራር የሆነው አቶ አንጋው ተገኝ ‹‹የተከሰስኩት ቤተሰቦቼን በእሳት አቃጠሉብኝ ብዬ ክስ በመመስረቴ ነው፡፡ ክሱን ካላቋረጥክ እናስርሃለን ሲሉ ቆይተው ነው ያሰሩኝ፡፡ የተከሰስኩበትን ወንጀል ፈፅሜ ሳይሆን ይህ ሰው ካለ አያስቀምጠንም ብለው ነው ያሳሰሩኝ፡፡ ፍርድ ቤቱን ከእነዚህ እየበደሉን ካሉ ሰዎች ጋር ቆሟል፡፡›› ሲል ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡

በሌላ በኩል የሰማያዊ ፓርቲ የአርባ ምንጭ ሰብሳቢ የሆነው አቶ በፍቃዱ አበበ መከላከያ ምስክር ለማቅረብ ልደታ ፍርድ ቤት ቀርቦ የነበር ቢሆንም ‹‹በሰዓት እጥረት›› ለነገ ሀምሌ 14/2007 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡ በተመሳሳይ በእነ ዘላለም ወርቃገኘው የክስ መዝገብ የተከሰሱት እነ የሽዋስ አሰፋ እንዲሁም በሰልፉ ሰበብ ይግባኝ የተጠየቀባቸው እነ ወይንሸት ሞላ በነገው ዕለት በልደታ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡ በተመሳሳይ እነ ብርሃኑ ተክለያሬድም ነገ በልደታ ፍርድ ቤት ከሰዓት እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.