የፌስቡኩ ምንስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሐኖም እና የኢትዮጵያ አርቲስቶች

መንበረ ካሳየ

” ከአንጋፋና ታዋቂ አርቲስቶች ጋር በሃገር ገጽታ ግንባታ በዲያስፓራ ንቅናቄና በሌሎችም ውጤታማ ውይይት አካሂደናል ። በጋራ ለመስራትም ተስማምተናል ። ” ይሉናል የፌስቡኩ ምንስትር ዶ/ር ቴድሮስ ..

እንደ ሙዚቃ የሚያዝናናኝ ምንም ነገር የለም ። ሙዚቃ ማለት ህይወት ነው ። በተለይ የሃገራችን ድምፃውያን ሰለ ሃገር ወገን ፍቅር ሲያቀነቅኑ ወይም ሰለ ፍቅር ሲያንጎራጉሩ ወደር አልነበራቸውም ። ዝነኛው ድምፃዊ ዶ/ር ጥላሁን ገሰሰ ( ነፍሱን ይማር እና ) አልቅሶ አስለቅሶናል ። ለተቸገረው ፣ ላዘነው ፣ ለተቀማው ፣ ለሃገሩ፣ ለወገኑ፣ ላፈቀረው እና በሞት ለተለየው …… ስንቱን ልግለፀው … በብዙሃን ልብ ውስጥ ገብቶ የዘላለም ቤቱን ሰርቶ አልፏል ።

በመንግስት ታዘዝን ፣ ይህን ዝፈኑ አለን ብለው ሰንቶቹ ያጉረመርሙ ነበር ። ሆኖም ግን የግለሰቦችን ልብ የሚነካ ወይም ቤት የሚያንኳኳ ጣል ሳያደርጉብን አልፈው አያውቁም ነበረ ። ለህዝብ ፍቅር የነበራቸው እና በርግጠኝነት ሃብታቸው ህዝብ መሆኑን ገብቷቸው ህዝብ ሚያገለግሉም ነበሩ ።

በአንድ ወቅት ህዝብ ለህዝብ የሚባል ቡድን የሃገራችንን ባህል ለዓለም ለማስተዋወቅ ( ይህ የኔ እይታ ነው ሰዎች ብዙ ምክንያት ሰተውታል ) ዝግጅት በሚያደርግበት ግዜ ዶ/ር ጥላሁንን አምኖ ወደ ውጭ ለመላክ ጭንቅ ሆኖ እንደነበረ ይነገራል ። በዛም የተነሳ የዶ/ር ጥላሁንን ሃሳብ ለማወቅ አንድ ሰው ይላክበት እና ጥላሁን ወደ ሃገር የመመለሱ ዋስትና እንዲረጋገጥ ይደረጋል ። በዚህን ግዜ ዶ/ር ጥላሁን ከሃገሬ ውጭ የኔ ኑሮ ሰማይቤት ነው በማለት ይናገር እና እንደወጣ እንደማይቀር ተረጋግጦ ቡድኑን ተቀላቅሎ ይሄዳል ። እንዳለውም ዶ/ር ጥላሁን ባመነበት የፀና ነበር ። እነ ጋሽ መሃሙድ ፣ ጋሽ ታምራት ሞላ ፣ ብዙነሽ ፣ ፀጋዬ እሸቱ ፣ ፀሃዬ ዮሃንስ በጣም በርካታ ዘፉኞች ሃብታቸው ህዝብ እንደሆነ አስመስክረዋል ።

አንድ ወጣት በዚህ በፌስቡክ ” የኢትዮጵያ አርቲስቶች ሃብታችሁ ሰንት ነው ሲባሉ ፣ ሃብታችን የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ይላሉ ። ታዲያ ሃብታችሁ የኢትዮጵያ ህዝብ ከሆነ ሲጠፋ ፣ ሲባክን እና ሲበተን ለምን ዝም ትላላችሁ ? ” ብላ ትልቅ የህሊና ጥያቄ አቅርባ ነበር ። ለዚህ መልስ የሰጣት አርቲስት አግኝታ እንደሆን አላውቅም ። ዛሬ አርቲስቶች ልማታዊ ናቸው ። መንግስትን ለማስደስት ደፋ ቀና የሚሉ ይበዛሉ ። ባለፈው ኢህአደግ 40 ዓመቱን ሲያከብር በቦታው በመገኘት ሳሞራ ላይ ተጠምጥማ ካመሸችው አርቲስት ሙሉዓለም አንስቶ ታላላቅ ልማታዊ አርቲስቶች የትግራይን ህዝብ ውለታ ከፍለን አንጨርሰውም ሲሉ ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን እኛንም ወክለው አድናቆታቸውን ገልፀዋል ። እኛም አይተን እና ሰምተን ታዝበናል ። ወደ ህዝብ ያደሉ ጥቂት ቢሆኑም እነሱም ቅጣት ይመሰል ለዝግጅት ከሃገር እንዳይወጡ እንቅፋት ይበዛባቸዋል ፕሮግራም ይሰረዝባቸዋል ። ታስረውም የተፈቱ እንዳሉ አውቃለሁ ።

የዘመኑ አርቲስቶች ከህዝብ ሳይሆን ህዝብን ደም እንባ ከሚያስለቅስ መግስት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲራመዱ ሳይ እኔም የቤቴን መደርደሪያ ያጣበበውን ሲዲያቸውን አውጥቼ ዱቄት አድርጌዋለሁ ።

አርቲስቶች የህዝ ናቸው ። ዘፈን ቢያወጡ ፣ ፊልም ቢሰሩ ፣ ድራማ ቢያሳዩ የሚገዛው እና ገብቶ የሚያያቸው ህዝብ ነው እና ከህዝብ ጋር ቢቆሙ ምን ያህል ክብር እንደሚያገኙ ያዩት ነበር ። ለማንኛውም እዚህ ላይ ይብቃኝ እና አንድ ቀልድ ተናግሬ ሃሳቤን ላጠቃልል ።

አርቲስት አረጋኸኝ ወራሽ Copyright በሚመለከት ክስ መስርቶ ዳኛው ፊት ይቀርባል ። ከሳሹ አረጋኸኝ ወራሽ መሆኑ ያስደነቃቸው ዳኛ ደግሞ ” ያንተን ዘፈን ማነው የሚያባዛው ” ብለው በመገረም ይጠይቁታል ። አረጋኸኝም በስጨት ብሎ ማባዛት ሳይሆን የኔን እየደመሰሱ በላዩ ላይ ይቀዱበታል አለ ይባላል ።

Menbere Kassaye

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.