በአርበኞች ግንባር አባልነት የተጠረጠሩ ዘጠኝ የሰሜን ጎንደር ነዋሪዎች በአሸባሪነት ተከሰሱ

–አንዱ ተጠርጣሪ የፌዴራል የፖሊስ አባል እንደነበር ተጠቁሟል

መቀመጫውን ኤርትራ ውስጥ ማድረጉንና ራሱን ‹‹የአርበኞች ግንባር›› በማለት እንደሚጠራ የተገለጸው ድርጅት አባል በመሆን፣ ተልዕኮ በመቀበልና አባላትን በመመልመል ሲሳተፉና ሲንቀሳቀሱ ተገኝተዋል የተባሉ ዘጠኝ የሰሜን ጎንደር ነዋሪዎች፣ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ መሳተፍ ወንጀል ሐምሌ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ሐምሌ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የመሠረተባቸው ለምለም የሺሬው፣ ገብረ ሚካኤል ገብረ ሥላሴ፣ አብዬ ተስፋዬ፣ እሸቴ ግርማዬ (የፌዴራል ፖሊስ አባል የነበረ)፣ ሀብታሙ ተረፈ፣ አታሎ ደለለኝ፣ ዶ/ር ባዬው አበራ፣ መልካሙ ታደሰና ኃይለ ማርያም ገነት ናቸው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ሐሪና ተብሎ በሚጠራው ማሠልጠኛ ተቋም ወታደራዊ ሠልፍና ሥልት፣ የጦር መሣሪያ አፈታትና አገጣጠም፣ የአካል ብቃት ትምህርትና ሥልጠና በመውሰድ፣ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም ዝግጅት ሲያደርጉ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ይገልጻል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ከመስከረም 3 ቀን 2007 ዓ.ም. እስከ ታኅሳስ ወር 2007 ዓ.ም. ድረስ የተለያዩ ኃላፊነቶችን በመውሰድ፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል የማፈራረስ ዓላማ ይዘው ኅብረተሰቡን ለማስፈራራት፣ የአገሪቱን የፖለቲካ፣ የሕገ መንግሥታዊ፣ የኢኮኖሚያዊ ተቋማትን ለማናጋትና ለማፈራረስ ከድርጅቱ ጋር ሲሳተፉ እንደነበር ክሱ ይጠቁማል፡፡

በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ደርሳ ቀበሌ ውስጥ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር በመዋጋት፣ የአማራን ሕዝብ ነፃ ማውጣት እንዳለባቸው በመነጋገር ምልመላ ማድረጋቸውንም ክሱ ይገልጻል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ስማቸውን በመቀየርና በሚስጥር ስም በመጠራራት፣ ስልክ በመደዋወልና የተለያዩ ዝግጅቶችን ለማድረግ ወደ ኤርትራ በመሄድ ላይ እያሉ፣ በተለያዩ ጊዜያት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተጠቁሟል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በአርበኞች ግንባር በመሰለፍ አባል በመሆን፣ ተልዕኮ በመቀበል፣ አባላትን በመመልመልና ድርጅቱን ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ ለመሄድ ሲሉ የተያዙ በመሆናቸው፣ በፈጸሙት በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በማናቸውም መልኩ መሳተፍ ወንጀል መከሰሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

እሸቴ ግርማይ የተባለው ተጠርጣሪ ከጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ በፌዴራል ፖሊስ አባል ሆኖ ሲሠራ ቆይቶ፣ ከጥር 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ የፖሊስ አባልነቱንና ግዴታውን ትቶ በመኮብለሉ፣ በኩብለላ ወንጀል ተጠርጥሮ መከሰሱን ክሱ ያስረዳል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ክሱ ደርሷቸው መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡና በሕግ ባለሙያ ጉዳያቸውን ለመከራከር የሚችሉበትን ሁኔታ ለመጠባበቅ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

Source:: Ethiopian Reporter

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.