መኢአድና አንድነት የቅድመ ውህደት ስምምነት ተፈራረሙ

-የፊርማው ሥነ ሥርዓት በብጥብጥ የታጀበ ነበር

1331ca5fdc1673aa8520bbf23f19d4e0_Lየመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ረዘም ላለ ጊዜ ሲያካሂዱት የነበረውን ድርድር አጠናቀው፣ ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው የመኢአድ ጽሕፈት ቤት የቅድመ ውህደት ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

የአንድነት ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራውና የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሀሪ የቅድመ ስምምነቱን አስመልክተው በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ሙሉ ውህደቱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚከናወንና አዲሱ ውህድ ፓርቲ ምክር ቤት 400 አባላት እንደሚኖሩት ገልጸዋል፡፡

የአዲሱን የውህድ ፓርቲ ስያሜን በተመለከተ ኢንጂነር ግዛቸው በስምምነቱ ላይ እንደተገለጸው የሁለቱንም ፓርቲዎች የቀድሞ ስያሜ ያቆራኘ አዲስ ስያሜ እንደሚወጣ አስረድተው፣ በሁለቱም ፓርቲዎች ዘንድ ‹‹አንድነት›› የሚለው ስያሜ የጋራ በመሆኑ እርሱን በመያዝ የቀድሞ ስሙን ሳይለቅ አዲስ ስያሜ ይወጣል ብለዋል፡፡ ዓርማውም በሁለቱ የጋራ ስምምነት የሚለወጥ መሆኑንና ይህም በውህዱ ፓርቲ አማካይነት እንደሚፀድቅ አብራርተዋል፡፡

በመጪው ዓመት በሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ የሚዋሀደው ፓርቲ ምን ዓይነት የምርጫ ስትራቴጂዎችን እንዳዘጋጀ በተመለከተ ከሪፖርተር ለቀረበው ጥያቄ ኢንጂነር ግዛቸው በሰጡት ምላሽ፣ በሚቀጥለው ዓመት ለሚካሄደው ምርጫ አጠቃላይ ስትራቴጂውን የውህዱ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ፣ ላዕላይ ምክር ቤት፣ ሥራ አስፈጻሚና ብሔራዊ ኮሚቴ የሚወስኑት ይሆናል ብለው፣ አሁን ውህደት እየተካሄደ ስለሆነ ሙሉ ለሙሉ ይኼ ነው ለማለት አስቸጋሪ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹ቢሆንም ሁለቱም ፓርቲዎች የምርጫ ፓርቲዎች በመሆናቸው ምን ጊዜም ለምርጫ እንዘጋጃለን፡፡ ነገር ግን በመጪው ዓመት ምርጫ መሳተፍ አለመሳተፋችን ወደፊት በሒደት የሚታይ ነው የሚሆነው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

ምርጫው ለይስሙላ መሆን የለበትም ያሉት አንጂነር ግዛቸው፣ ምርጫው በተቻለ መጠን አንፃራዊ በሆነ ሁኔታ የዲሞክራሲ ተቋማት ማለትም የምርጫ ቦርድ፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የፍትሕ መዋቅሩና አካላት፣ ሲቪል ማኅበረሰቡና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸው ነፃ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡

‹‹እነዚህ ተቋማት ነፃ ከሆኑ እንሳተፋለን፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ቢሆንም ይህ አስቸጋሪ ሁኔታ አይፈታም አይባልም፡፡ ይህን የማስተካከል ዕድል አለ ብዬ አምናለሁ፤›› በማለት ተስፋና ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

በሽማግሌዎች ግፊት ነው ከዚህ ስምምነት ላይ የደረሳችሁት ተብለው የተጠየቁት ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች፣ ይህ ከእውነት የራቀና የሁለቱን ፓርቲዎች የውህደት ታሪክ ካለማወቅ የመጣ ነው ብለዋል፡፡

አንድነትና መኢአድ የመዋሀድ ድርድር የጀመሩት ከአራትና ከአምስት ዓመታት በፊት መሆኑን ጠቅሰው፣ አደራዳሪ የተባሉት ሽማግሌዎች ግን የመጡት ባለፈው ጥር ነው ካሉ በኋላ፣ ‹‹አመጣጣቸውም ቢሆን ለማደራደር ሳይሆን ቀደም ብለን የጀመርነውን ድርድር ስለሚያውቁ ለአገር ይጠቅማል ግፉበት ለማለት ነው፤›› በማለት ፕሬዚዳንቶቹ በጋራ አብራርተዋል፡፡

‹‹በቅድመ ውህደት ስምምነቱ ላይ የውስጥ ችግራችንን ሳንፈታ ወደ ውህደት መሄድ የለብንም፤›› በማለት ተደራጅተዋል የተባሉ የመኢአድ አባላት የውህደት ሥነ ሥርዓቱን ከማወካቸውም በተጨማሪ፣ የአንድነት ፓርቲ የሒሳብ ክፍል ኃላፊና የውህደት ኮሚቴ አባል አቶ ፀጋዬ አላምረው ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ከእሳቸው በተጨማሪ የመኢአድ የመሀል ቀጣና ኃላፊና የሥራ አስፈጻሚ አባል በሆኑት አቶ ደመላሽ ካሳዬ ላይም ድብደባ ደርሶባቸዋል፡፡

በዕለቱ የተፈጠረውን ብጥብጥ የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሀሪ የኢሕአዴግ የአዲስ አበባ አባላትና የደኅንነት አባላት ሥራ ነው በማለት የገለጹ ሲሆን፣ ‹‹የውስጥ ችግራችሁን ሳትፈቱ ማለት የሚችሉት የመኢአድ አባላት እንጂ ሌሎች ግለሰቦች መሆን የለባቸውም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ይህ ደግሞ ገዥው ፓርቲ አገሪቱ ውስጥ ጠንካራ ፓርቲ እንዳይፈጠርና የጭቆና ቀንበሩን በሕዝቡ ላይ ለመጫን ያለውን ፍላጐት ማሳያ ነው፤›› በማለት በዕለቱ የተከሰተው ብጥብጥ ከመኢአድ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው አስታውቀዋል፡፡

በዕለቱ በተፈጠረ ብጥብጥ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው የነበረ ሲሆን፣ የአንደኛው ኪስ ሲፈተሽ ለአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት የአባልነት ወርኃዊ መዋጮ የከፈለበት ደረሰኝ የተገኘ መሆኑን፣ ግለሰቡም ለሰዓታት በመኢአድ ጽሕፈት ቤት ከቆየ በኋላ ‹‹የሠራሁት ሥራ ስህተት ነው›› ብሎ በማመኑ መለቀቁን የአንድነት ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ለምን ክስ እንዳልመሠረቱ ተጠይቀው፣ ‹‹ብንከሳቸውም ፍትሕ እናገኛለን ብለን አናምንም፡፡ ስለዚህ ጥፋታቸውን በማመናቸውና ይህንኑ ቀድተን በማስቀመጥ ለቀናቸዋል፤›› በማለት መልሰዋል፡፡

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው አቶ ፀጋዬ አላምረው የላይኛው ከንፈራቸው ከመሰንጠቁም በተጨማሪ፣ በሁለት ጥርሶቻቸውም ላይ ተመሳሳይ የመሰንጠቅ አደጋ መድረሱን አቶ ሀብታሙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሁን ከንፈራቸው የተሰፋ በመሆኑ ጥርሶቻቸው ለጊዜው ታስረው ቆይተው የከንፈራቸው ቁስል ከደረቀ በኋላ የሚታይ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በጥርሶቻቸው ላይ ከፍተኛ አደጋ ነው የደረሰው፤›› ብለዋል፡፡

Source: Ethiopian Reporter

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.