በሀገራችን ሴክስ ቱሪዝም እንደ ሰደድ እሳት እየተስፋፋ ነው

ወደድንም ጠላንም በሀገራችን ሴክስ ቱሪዝም እንደ ሰደድ እሳት እየተስፋፋ ነው፡፡ በአዲስ አበባና በተለያዩ የሀገራችን የከልል ከተሞች ይህንን ግልጋሎት ልክ እንደምግብና መጠጥ ወደ ሜኗቸው አካተው ለደምበኞቻቸው የሚያቀርቡ ሆቴሎች በርካቶች እንደሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

እዚሁ መቐለ ውስጥ እንኳን በዚህ ስራ የተሰማሩ አራት ሆቴሎች እንዳሉ ተሰምቷል፡፡ አዲስ አበባ፣ አዋሳ፣ አዳማ ደግሞ ሁኔታው ከዚህም የባሰ ነው፡፡ እነዚህ ሆቴሎች የበርካታ ሴት የዩነቨርሲቲ ተማሪዎች አድራሻና ፎቶ ያላቸው ሲሆን ወንድ ደምበኞቻቸው ሲመጡ የነዚህን ተማሪዎች ፎቶ ጋለሪ በማሳየት እንዲመርጡ በማድረግና ተማሪዎቹ በማስጠራት ግልጋሎቱን እንዲያገኙ ያደርጋሉ፡፡ ከዚህም ላቅ ያለ ኮሚሽን ያገኛሉ፡፡
መቐለ መሐል ከተማ ላይም በግላጭ ይህንን ስራ የሚሰራ በስመ “የኮስሞቲክስ እቃዎች መሸጫ” የተቋቋመ ድርጅት መኖሩንና በሩ ላይ በጉልህ PIMP የሚል እንደተፃፈበት ያወቅኩት በቅርቡ ነው፡፡ አስገራሚ ነው!
አሁን አሁን ኢትዮጵያ በዚሁ የሴክስ ቱሪዝም እንደሚታወቁ እንደ ታይላንድ፣ ፊሊፒንስ፣ ካምቦድያ ወ.ዘ.ተ አንዷ እየሆነች እንዳለና አዲስ አበባም በብዙዎቹ የአፍሪካ መሪዎች ለሰብሰባ ለመመረጧም ዋናው ምክንያት ይህ እየሆነ እንዳለ መረጃዎች አሉ፡፡

ሰብሰባዎችና እንግዶች በመጡ ቁጥር “እንግዶች እንዲቀበሉ”ና “አገር እንዲያስጎበኙ” ተብለው ተመርጠው አልጋ ተይዞላቸው ከእንግዶቹ ጋር ወዲያ ወዲህ ሲሉ የሚታዩት ዋና ግዳጃቸው ይህ የሴክስ አቅርቦት ማሟላት እንደሆነ የሚወሩ ወሬዎች አሉ፡፡ እዚሁ መቐለ እንኳን ባለፈው ዐመት በተለያዩ ጊዜያት እንግዶች በተለይም ዲያስፖራዎች እንዲቀበሉ ተብለው ሆቴል ተይዞላቸው ይህንን ግልጋሎት የሚሰጡ ጨቅላ ልጆች እንደነበሩ መረጃዎች አሉ፡፡

ይህ በሀገራችን እየተፈፀመ ያለው ነውር ከባህላችን፣ ከሀይማኖታችን ያፈነገጠና ለብዙዎች በተለያዩ በሽታዎችና ሱሶች መጠቃት ምክንያት እየሆነ ከመሆኑ በላይ ለዚህ ነውራም ተግባር በጨቅላ ሴት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየተደረገ ያለ መሆኑ ነው፡፡ እንደመረጃዎቹ የብዙዎቹ እድሜ ከ17-21 ዐመት እድሜ ክልል ያለ ነው፡፡ ዛሬ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ከእውቀት ማእድነታቸው በላይ የሽርሙጥና ማስፋፊያታቸው እየጎላ ነው፡፡
በተግባሩ ተሳታፊዎችም ተመልካቾችም ሁሉም ላይ ከባድ የስነ-ልቦና ጫና እየሳደረና ዩኒቨርሲቲዎቻችን ጥፋታችን የሚጠነሰሱበት ማእከላት እየሆነ ነው፡፡ ይህ በአጭርና በረጅም ጊዜ ትውልዳችንን ሊያጠፋ የሚችል ነው፡፡
ትንሽ ዶላር ለመለቃቀም ተብሎ ትውልድ እየጠፋ ነውና ይህንን በዝምታ ልናልፈው የሚገባ አይደለም፡