የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር በአዲስአበባ ከተማ መቀነስ ያልቻለው መመሪያዎችን በቁርጠኝነት መፈጸም የማይችል አመራር በመኖሩ ነው አሉ

ድሪባ ኩማ – የአዲስ አበባ ከንቲባ

የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባና የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ኮምቴ አባል አቶ ድሪባ ኩማ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር በከተማዋ መቀነስ ያልቻለው መመሪያዎችን በቁርጠኝነት መፈጸም የማይችል አመራር በመኖሩ ነው ሲሉ በስራቸው የሚገኙ አመራሮችን ወቅሰዋል፡፡ ከንቲባው ይህን የተናገሩት በሰኔ ወር 2007 የተጠናቀቀውን የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸምና በቀጣይ ዓመት የሚጀምረው ሁለተኛውን ዕቅድ አስመልክቶ ከከፍተኛ አመራሮች ጋር ሰሞኑን በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡ በከተማ አስተዳደሩ በሳምንት ሁለት ጊዜ የሚታተመው «አዲስ ልሳን» ጋዜጣ በትላንት ዕትሙ እንደዘገበው ከንቲባው ባለፉት አምስት ዓመታት በአስተዳደሩ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር በታሰበው መልኩ አለመቀነሱን አረጋግጠዋል፡፡ ለዚህ ምክንያት ነው ያሉት ደግሞ በየደረጃው ያሉ አንዳንድ አመራሮች የሚወጡ መመሪያዎችን ማስፈጸም ባለመቻላቸው ነው፡፡ ከንቲባው በቁጥር ቀላል የማይባሉ አመራሮች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ፈጻሚዎች ከመመሪያ ውጪ ሲሰሩ በዝምታ በማለፍ፣ ራሳቸውም አልፎ አልፎ ተሳታፊ በመሆን ኪራይ ሰብሳቢነት በከተማዋ እንዲስፋፋ በር ከፍተዋል ከማለታቸውም በተጨማሪ፣ አንዳንድ የአስተዳደሩ መ/ቤቶችም የሚመሩት በአመራሮቹ ሳይሆን በደላሎች ፍላጎት ነው ብለዋል፡፡ ከንቲባው አንዳንድ ፈጻሚና አመራር ባልተገባ ጥቅም የተሳሰሩ በመሆናቸው አንዱ የህዝብ ንብረት ሲዘርፍ ሌላው በዝምታ የሚመለከትበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመውዋል፡፡ የተቋማት ውጤትም ሆነ ውድቀት በዋናነት የሚወሰነው በአመራሩ ጥንካሬና ድክመት ነው ያሉት ከንቲባው፣ አመራሩ ፈጻሚዎች የሚያከናውኑዋቸውን ተግባራት በትክክለኛው መንገድ መስራታቸውን መከታተል አለባቸው ብለዋል፡፡

Source:: Ethsat

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.