ቤተ ክርስቲያን አማሳኞችን አሳልፋ እንደምትሰጥ ፓትርያርኩ ለዋና ሥራ አስኪያጁ አረጋገጡ፤“ለማንም ከለላ አልኾንም፤ ለአንተም ጭምር”

  • አማሳኝ ሓላፊዎች፤ በካህናት እና ሠራተኞች ስም የሚያቀርቡት አቤቱታ ተቀባይነት የለውም
  • ከብፁዕ ዋ/ሥራ አስኪያጁ ጀምሮ ብፁዓን አባቶች ለማስፈራራትና ለመደለል እየተሞከረ ነው
  • “እጁ የተገኘበትን ኹሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ አሳልፋ ትሰጣለች፤ ይኼ የመጨረሻ አቋሜ ነው”

/ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ/

* * *

ጉቦ መስጠት ይኹን ጉቦ መቀበል፤ በጎሰኝነት እና ጥቅመኝነት ላይ የተመሠረተ ቅጥር፣ ዕድገት እና ዝውውር መፈጸም፤ በልማት ስም ምዝበራ እና ዘረፋ ማጧጧፍ በሃይማኖታዊ አስተምህሮ ለኩነኔ የሚዳርግ ኃጢአት ከሕግም አኳያ የሚያስቀጣ ወንጀል እንደኾነ ይታወቃል፡፡

በስፋት እና በተደጋጋሚ እንደሚነገረው፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ “የሥነ ምግባር እና የፀረ ሙስና አስተሳሰቦችን በምእመናን ዘንድ በማስፋፋት ሙስናንና ብልሹ አሠራርን የሚጸየፍ ዜጋ ለማፍራት” ከሌሎች የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት የላቀ ድርሻ አላቸው፤ ከቆሙለት ዓላማ አንጻር የሥነ ምግባር (የሞራል) ጉዳይ ዋነኛ ትኩረታቸው ነውና፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ባሏት ብዙ ሚሊዮኖች ካህናት እና ምእመናን ሙስናን ለመዋጋት እና ሥነ ምግባርን ለማስፋፋት የምታበረክተው አገራዊ አስተዋፅኦ ጉልሕ እና ከፍተኛ ነው፡፡ የሙስናን አጸያፊነት በግልጽ ቋንቋ ከማስተማር ባሻገር በተግባርም ራስን ከተወገዙ መጥፎ ተግባራትና ከሕገ ወጥ ድርጊቶች በማራቅ በአርኣያነት መታየት፣ በምእመኑ ዘንድ ተቀባይነትንና ተአማኒነትን በማጎናጸፍ ማኅበረሰቡን ለመለወጥ የሚያበቃ ጉልበት ለማግኘት ያስችላል፡፡

በአስተዳደር ሓላፊዎችና ሠራተኞች መካከል፤ የሥነ ምግባር ብልሹነት በዝቶ፣ የሙስና ወንጀል ተንሰራፍቶና የአገልጋዮቻችን ሞራላዊ ልዕልና ተሸርሽሮ÷ የጥንታዊትና ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ ዕድገት እና ጉልሕ ማኅበራዊ ሚና አደጋ ላይ ከወደቀ የቤተ ክህነታችን አመራር እና አስተዳደር የታሪክ ተወቃሽ እና ተጠያቂ ከመኾን አይድንም፡፡

ከቤተ ክርስቲያናችን መሠረታዊ ተልእኮ ጋር ያልተቀናጀው፤ ከችሎታ፣ ዕውቀትና ልምድ ይልቅ በወገንተኝነት እና ሙስና የተሞላው እና የተለያዩ የሥነ ምግባር ብልሽቶች የሚንጸባርቅበት የወቅቱ የቤተ ክህነታችን አስተዳደር አስቸኳይ እና ቆራጥ የለውጥ ርምጃሊወሰድበት እንደሚገባ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡

የቅዱስነታቸውን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ለማድረግ በመንበረ ፓትርያርክ ደረጃ በባለሞያዎች የተዘጋጀው የመሪ ዕቅድ ጥናት፣ ሙስናንና ለብክነት የተጋለጡ አሠራሮችን፣ ዘመኑን ያልዋጀ የፋይናንስ አያያዝንና የመልካም አስተዳደር ዕጦትን በወሳኝ መልኩ ከሥሩ ለመቅረፍ እንደሚያስችል ያመነበት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤም፣ በሥራ ለመተርጎም በሚያስችል አኳኋን የመጨረሻ መልኩን ይዞ እንዲቀርብለት ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ደረጃም ለተጠናው የመዋቅር፣ የአደረጃጀት እና የአሠራር መመሪያ ጥናት፤ ምልአተ ጉባኤው በሰጠው ይኹንታ እና የአፈጻጸም አቅጣጫ መሠረት በማኅበረ ካህናት፣ በማኅበረ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች ውይይት ከተካሔደበት በኋላ እጅግ ከፍተኛ ተቀባይነት ቢያገኝም ትግበራው ሕገ ጥቅማቸውን በሚያስተጓጎልባቸው አማሳኞች ተሰነካክሎ ይገኛል፡፡

በመልካም አስተዳደር፣ በፋይናንስ አያያዝ፣ በስብከተ ወንጌል እና በአገልግሎት አሰጣጥ ሀገረ ስብከቱን ለሌሎች አህጉረ ስብከት በሞዴልነት የሚጠቀስ እንደሚያደርገው የታመነበት ጥናት፣ አማሳኝ የአድባራት ሓላፊዎች በፈጠሩት ተጽዕኖ ትግበራው መስተጓጎሉ የፓትርያርኩን ቁርጠኝነት ጥያቄ ውስጥ ከቶት ቆይቷል፡፡ ሀገረ ስብከቱ፣ በሰው ኃይል አመዳደብ እና በፋይናንስ አያያዝ የሕግ የበላይነትን አክብሮ እንዲሠራ አስፈላጊውን ክትትል እንዲያደርጉ በግንቦት ፳፻፭ ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የታዘዙትን የቋሚ ሲኖዶሱንና የመንበረ ፓትርያርኩን የማስፈጸም አቅምም ለትችት ማጋለጡ አልቀረም፡፡

ይኹንና በ58 የሀገረ ስብከቱ አድባራት እና አንዳንድ ገዳማት የመሬት፣ የሕንጻ እና የልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ተቋማት ኪራይ ተመንላይ ላለፉት ስድስት ወራት ሲካሔድ የቆየው ጥናት በሐምሌ መጨረሻ ለውሳኔ መብቃቱን ተከትሎ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በአማሳኝ የአስተዳደር ሓላፊዎች ላይ የያዙት ቁርጠኛ አቋም፣ ለቤተ ክርስቲያን መብቶች እና ጥቅሞች መጠበቅ ከምር የሚቆረቆሩ ወገኖችን ተስፋ አለምልሟል፡፡

ፓትርያርኩ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ፣ በቋሚ ሲኖዶስ በማስወሰን ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአስተዳደር ጉባኤ በሰጡት ትእዛዝ የተቋቋመው ኮሚቴ ሐምሌ ፳፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ያቀረበው ጥናታዊ ሪፖርትቤተ ክርስቲያኒቱ ያለችበትን ተጨባጭ ኹኔታ የሚያመለክት፤ ንብረቶቿን በአስተማማኝ ኹኔታ ለመጠበቅ እና በሀብቷ የሚነግዱ ወገኖች ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ እንደኾነ” ታምኖበታል፡፡ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ሰብሳቢነት የሚመራው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር ጉባኤም ሪፖርቱን በስፋት ከተወያየበት በኋላ በሙሉ ድምፅ በመቀበል ባለዐሥር ነጥብ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

ዕለቱን “እንደተወለድኩባት ቀን እቆጥረዋለኹ” በማለት በጥናታዊ ሪፖርቱ ደስታቸውን የገለጹት ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣የኮሚቴው አባላት ስም ማጥፋትን ጨምሮ ብዙ ውጣ ውረድ እና ፈተና በማለፍ ለከፈሉት መሥዋዕትነት እና ገድል በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም አወድሰዋቸዋል፤ አማሳኞች የሚገባውን ቅጣት ያገኛሉ፤ ማንም ምንም ቢል ይህን ነገር ከዳር አደርሳለኹ”ማለት “የፀረ ሙስና ተጋድሎውን በወቅቱ ለተቀላቀሉ” የአስተዳደር ጉባኤው አባላት ቁርጠኝነታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በተ.ቁ(፱) ላይ የሰፈረው የአስተዳደር ጉባኤው የውሳኔ ሐሳብ፣ በጥናቱ የተጠቀሱ ከፍተኛ እና ዝቅተኛ ችግሮች በባለሞያ ተጠንተው እና ከሕግ አንጻር ተገምግመው በቤተ ክርስቲያኒቱ ንብረቶች አለአግባብ ሀብት ያፈሩና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ለምዝበራ ያጋለጡ የአድባራት ሓላፊዎች ያጠፉት ጥፋት እየተመዘነ በሕግ አግባብ ጉዳያቸው እንዲታይና ክሥ እንዲመሠረትባቸው እንዲደረግ፤ ይላል፡፡ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ከአስተዳደር ጉባኤው አባላት ጋር በመኾን ጥናታዊ ሪፖርቱንና የውሳኔውን ቃለ ጉባኤ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ባቀረቡበት ወቅት የተሰጠው ምላሽም በውሳኔው መሠረት የአማሳኞችን የሕግ ተጠያቂነት አይቀሬነት ያረጋገጠ ነበር፡፡

ይኹንና በተለይም ከፍተኛ ችግር እንዳለባቸው የተጠቀሱት አድባራት ሓላፊዎች፣ በቀንደኛው አማሳኝ ኃይሌ ኣብርሃ አስተባባሪነት፣ ዘካርያስ ሐዲስ ባለበት የኮተቤ ደ/ጽባሕ ቅ/ሚካኤል እንዲኹም በየካፌው እና በየሆቴሉ በመሰብሰብ እንደለመዱት አፈጻጸሙን ለማሰናከል እየዶለቱ ይገኛሉ፡፡ በተቃውሟቸው ካህናቱንና ልዩ ልዩ ሠራተኞችን በማስፈራራትም በመደለልም ከጎናቸው ለማሰለፍ እየጣሩ ሲኾን በአንዳንድ ፕረሶችም የጥናታዊ ሪፖርቱን ይዘት እና የኮሚቴውን አባላት ለማጥላላት መሞከራቸው አልቀረም፡፡

አማሳኞቹ፣ ጥናቱን ለማስተባበል እና በማጣራቱ ሒደት ግንባር ቀደም ሚና የነበራቸውን የኮሚቴው አባላት ለማጥቆር በሞከሩ ቁጥር፣ ዘራፊነታቸውንና መዝባሪነታቸውን ይበልጥ እያረጋገጡ ይገኛሉ፡፡ በእነ ኃይሌ ኣብርሃ እና የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ አመራር፣ በዲዛይን ማሻሻያ የ100 ሚሊየን ብር ልዩነት ስለታየበት የሕንጻ ግንባታ በሰንደቅ ጋዜጣ የሰፈረው የደብሩ ሓላፊዎች ምላሽ ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡

የአማሳኞቹ ግንባር ቀደም መሪዎች፣ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁን ከማስፈራራት እና የአስተዳደር ጉባኤ አባላቱንም ለመከፋፈል እየሠሩ ነው፤ ሥራውን ከነገ በስቲያ የሚጀምረው ቋሚ ሲኖዶስም ዛሬ፣ ነሐሴ ፲፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በፓትርያርኩ በተመራለት የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ጥናታዊ ሪፖርት እና ውሳኔዎች ላይ ይኹንታውን ከመስጠቱ በፊት የወቅቱን ተለዋጭ አባላት ቀራቢዎች ነንበሚሉ ግለሰቦች ለመደለል መንቀሳቀስም ይዘዋል፤ ለዚኽም የአድባራቱን ተቀማጭ በሥራ ማስኬጃ ስም ወጪ በማድረግ እና በዘረፋ ያካበቱትን ገንዘብ በመርጨት ላይ ይገኛሉ፡፡

የአማሳኞቹ ግንባር ቀደም አስተባባሪዎች ከሚያደርጉት ግፊት በአንጻሩ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ እና ለአስተዳደር ጉባኤ አባላቱ ባረጋገጡት አቋም እንደጸኑ ናቸው፡፡ ቅዱስነታቸው፣ በትእዛዛቸው መሠረት በተካሔደው እና የፀረ ሙስና አቋማቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ታላቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው በታመነበት ጥናት የተዘረዘሩ የመፍትሔ ሐሳቦችን፤ በጥናታዊ ሪፖርቱ መነሻነት የተላለፉ የጠቅላይ ጽ/ቤቱን ውሳኔዎች ለማስፈጸም “በቤተ ክርስቲያን ሀብት ከመዝባሪዎች ጋር አልደራደርም፤ ወደ ግራ ወደ ቀኝ የለም፤ ወደፊት ነው” ብለዋል፡፡

በቀንደኛው እና ልማደኛው አማሳኝ ኃይሌ ኣብርሃ እና የሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅነትን ከደብር ዋና ጸሐፊነት ጋር ደርበው በያዙት የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ማስፈራሪያ እና ተጽዕኖ ‘ለአቤቱታ’ ለመጡ ካህናት እና ልዩ ልዩ ሠራተኞች የሰጡት ምላሽ፣ ሒደቱ በሕግ አግባብ የሚመዘን እንጂ በአሉባልታ ጋጋታ እንደማይገለበጥ ከማረጋገጥ አልፎ በካህናቱ ጀርባ የተደበቁትን እነኃይሌ ኣብርሃን የሚገሥጽም ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ፣ የአማሳኞቹ መልእክተኛ በመኾን በዋና ሥራ አስኪያጅነት ካባ ለቀረቡት የማነ ዘመንፈስ ቅዱስም ‹‹ለማንም ሰው ከለላ መኾን አልፈልግም፤ ሽፋንም አልሰጥም፤ ለአንተም ጨምሮ፤›› በማለት ነው የፍትሕ ጎማ መሽከርከር መጀመሩን ያስታወቁት፡፡


(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፭ ቁጥር ፰፻፲፬፤ ቅዳሜ ነሐሴ ፲፮ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

በቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብት፣ ዘረፋ እና ምዝበራ ጥፋታቸው በማጣራት የተረጋገጠባቸው የአድባራት እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አማሳኝ ሓላፊዎች ለሕግ ተጠያቂነት ተላልፈው እንደሚሰጡ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ተናገሩ፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች እንደጠቆሙት፣ ፓትርያርኩ ይህን የማረጋገጫ ቃል የተናገሩት፣ ስለ አድባራቱ የመሬት፣ የሕንጻ እና የልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ተቋማት ኪራይ ተመን በተካሔደው ጥናታዊ ሪፖርት ላይ የሀገረ ስብከቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስን ባለፈው ማክሰኞ ጠዋት በጽ/ቤታቸው ባነጋገሩበት ወቅት ነው፡፡

ጥናታዊ ሪፖርቱ፣ ‹‹አድሏዊ እና ግለሰቦችን ለማጥቃት የተደረገ ነው›› በሚል በአንዳንድ አድባራት ተቃውሞ ማስነሣቱን ዋና ሥራ አስኪያጁ ለፓትርያርኩ ጠቅሰዋል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር ጉባኤ፣ የጥናታዊ ሪፖርቱን የመፍትሔ ሐሳቦች በሙሉ ድምፅ በመቀበል፣ የአድባራቱ ሓላፊዎች ጥፋት በሕግ አግባብ እንዲታይና ክሥ እንዲመሠረትባቸው ያሳለፈው ውሳኔም ሌላ አማራጭ እንዲፈለግለት ፓትርያርኩን ጠይቀዋልም ተብሏል፡፡

ጥናቱ፣ ራሳቸው በሰጡት ትእዛዝ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር ጉባኤ ባቋቋመው ኮሚቴ በይፋ መካሔዱን ያስታወሱት ፓትርያርኩ፣ ሪፖርቱን ለመቃወም በሚል ካህናትንና ልዩ ልዩ ሠራተኞችን በተለያዩ መንገዶች በማደራጀት በጎን የሚቀርብላቸውን አቤቱታ እንደማይቀበሉት ለዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

His Holiness warning the GM Yemane‹‹ለማንም ሰው ከለላ መኾን አልፈልግም፤ ሽፋንም አልሰጥም፤ ለአንተም ጨምሮ፤›› በማለት አቋማቸውን ያረጋገጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ‹‹በዚኽ አጸያፊ የዘረፋና የምዝበራ ሥራ ውስጥ እጁ የተገኘበትን ሰው ኹሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ አሳልፋ ትሰጣለች፤ ይኼ የመጨረሻ አቋሜ ነው፤›› ሲሉ የሕግ ተጠያቂነቱ አይቀሬ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡

በፓትርያርኩ ጠንካራ አቋም መደናገጥ ታይቶባቸዋል የተባሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ በሀገረ ስብከቱ ተከማችተው ለቆዩትና በየአድባራቱ እየተባባሱ ለመጡት የሙስና እና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ችግሮች የአሠራር ማሻሻያዎች በመተግበር ላይ እንደሚገኝ በማስረዳት ጥናታዊ ሪፖርቱን እንደሚቀበሉትና እንደሚደግፉት ለፓትርያርኩ ማረጋገጣቸው ታውቋል፡፡

ላለፉት ስድስት ወራት በ58 አድባራት ላይ ሲካሔድ የቆየው ጥናት፣ ከሓላፊዎቹ ጋር የጥቅም ትስስር ለፈጠሩ ግለሰቦች በሚያደሉ ውሎች በቤተ ክርስቲያኒቱ መሬት፣ ሕንጻዎች፣ ሱቆች እና ልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛ ተቋማት ላይ የተጧጧፈ ዘረፋና ምዝበራ መፈጸሙን አረጋግጧል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብትና ንብረቷን ከብክነት ለመታደግ ያወጣችውን የቃለ ዐዋዲ ደንብ ማስከበር የሚገባው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም፤ ከድንጋጌው ውጭ ለተሠሩ ሥራዎች ዕውቅና በመስጠት የሕግ ጥሰቱ አካል እንጂ የሕግ አስፈጻሚ መኾን አለመቻሉ የችግሩ ባለቤት እንደሚያደርገው በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በፓትርያርክነት በተመረጡበት በዓለ ሢመት፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ የሚታዩ አንዳንድ የሙስና ሒደቶችን ለማስወገድ የገቡትን ቃል መነሻ በማድረግ የተካሔደው ጥናቱ፣ የፀረ ሙስና አቋማቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር ጉባኤ በውሳኔው አመልክቷል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከአስተዳደር አኳያ ያለችበትን ተጨባጭ ኹኔታ የሚያመለክት በመኾኑም ጥናቱን መነሻ ያደረገ የፀረ ሙስና እንቅስቃሴ በማድረግ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር ወደ ጥንቱ ጊዜ ለመመለስ በግንባር ቀደምነት እንደሚሰልፍም አስታውቋል፡፡

Source:: haratewahido

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.